ትግራይ፡ መንግሥት በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታን የሚያስተጓጉል ችግር የለም አለ

በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማቀረብ የሚደረገው ጥረት በውጊያ ምክንያት እንደተስተጓጎለ የሚነገር እውነት እንዳልሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በክልሉ በሚገኙ "በርካታ ከተሞችና በዙሪያቸው ባሉ አካባቢዎች በሚካሄድ ውጊያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራው እንቅፋት እንደገጠመው ተደርጎ የሚነገረው ሐሰት" እንደሆነ ገልጾ ይህም በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለማረጋጋት የተከናወኑ ወሳኝ ተግባራትን የሚቃረን ነው ብሏል።

ጨምሮም በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት እየሸሹ ያሉ የወንጀለኛው ቡድን አባላትን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አልፎ አልፎ ከታጣቂዎች ጋር የሚደረግን የተኩስ ልውውጥን እንደ ውጊያ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ አመልክቷል።

የተባበሩት መንግሥታት በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ከኢትዮጵያ መንግሥታ ጋር ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ ትግራይ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በሚካሄድ ውጊያ ምክንያት እርዳታ ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት እንደተስተጓጎለበት ባለፈው ሳምንት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል መግለጹ ይታወሳል።

ጨምሮም ለሳምንታት በዘለቀው ግጭት ሳቢያ በርካታ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ አቅርቦት መሟጠጡን በመግለጽ እርዳታውን ለሚፈልጉ ዜጎች ለማድረስ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ቢደረስም ወደ አካባቢዎቹ መድረስ እንዳልቻሉ ገልጾ ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ [አርብ] ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ለሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታዎች አቅርቦት አስተማማኛና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሶ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የአቅርቦት መስመሮች እንደሚመቻቹ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት ዓለም አቀፍ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው በትግራይ እንደተገደሉባቸው አስታውቋል።

ዳኒሽ ሪፊውጂ ካውንስል እና ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ (አይአርሲ) ዛሬ እና ትናንት ባወጡት መግለጫ በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ባልደረቦቻችን ተገድለዋል ብለዋል።

ዳኒሽ ሪፊውጂ ካውንስል ባሳለፍነው ወር ሦስት የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞቹ መገደላቸውን ሲያስታውቅ ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ (አይአርሲ) በበኩሉ በሽሬ ከተማ ህጻጽ የሰደተኞች መጠለያ ካምፕ ይሰራ የነበረ ባልደረባው መገደሉን አስታውቋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት መንግሥት የዜጎቹን ደኅንት በሁሉም በኩል ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጾ በትግራይ ክልል ያሉና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች አስፈላጊው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ እንደሚሰራ፤ ነገር ግን ከዚህ ተቃራኒ የሚወጡ ሪፖርቶች የፌደራል መንግሥቱን ጥረት ለማሳነስ በሚካሄድ የተሳሳተ መረጃ የማሰራጨት ዘመቻ ምክንያት ነው ብሏል።

የእርዳታ አቅርቦቱ በተገቢው ሁኔታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እንዲደርስ ከተመድ ጋር በተደረሰው ስምምነት በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት አላማ፣ መርህ፣ የአቅርቦት ቅንጅት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ላይ ከስምምነት ተደርሶ በዚሁ መሠረት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመለክቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንዳለው ከሳምንታት በፊት ጀምሮ ሠራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የመሠረታዊ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቶች በመንግሥት አማካይነት ሲቀርብ መቆየቱን አመለክቶ አሁንም የክልሉን ዋና ከተማን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች የምግብና የመድኃኒት ድጋፎች እየቀረቡ መሆኑን አመለክቷል።

ከሳምንታት በፊት በአንዳንድ አካባቢዎች የእርዳታ አቅርቦት መዘግየት አጋጥሞ እንደነበረ አመለክቶ መቀለ ከተያዘች በኋላ ግን ወታደራዊው ዘመቻ አብቅቶ ተፈላጊ "የወንለኛ ቡድኑ አባላትን" የመያዝ ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ የእርዳታ አቅርቦቶች እየተከፋፈሉ መኖናቸውን ገልጿል።

በዚሁም መሠረት በመጀመሪያው ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ ወደ ዳንሻ፣ ወልቃይት፣ ቃፍታ፣ ሁመራና ደባርቅ አካባቢዎች መላካቸውን እንዲሁም ባለፈው ሳምንት 18 ሺህ 200 ኩንታል የምግብ ድጋፍ የያዙ 44 ካባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለማከፋፈል ወደ ሽረ መላካቸው ተነግሯል።

በተጨማሪም 5500 ኩንታል የምግብ ድጋፍ ወደ አላማጣ፣ 7 ሺህ ኩንታል ዱቄት እና 12ሺህ 500 ኩንታል የምግብ ድጋፍ ወደ መቀለ እንደተላከ እንዲሁም የህክምና ግብዓቶች ወደ መቀለ፣ ሽረና አዲግራት ከተሞችም መላካቸው ተገልጿል።

በትግራይ ክልል በሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ በክልሉ እለታዊ የመሠረታዊ ፍላጎት አቀርቦት መስተጓጎሉ ይታወቃል።

በዚህም ሳቢያ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን የምግብና የመድኃኒት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት ቢያደርጉም እንቅፋት እንዳጋጠማቸው ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል።

ለሳምንታት በዘለቀው ወታደራዊ ግጭትን ተከትሎ በርካቶች የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተገለጸ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ግጭቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መግባታቸውን የእርዳታ ድርጅቶች አመልክተዋል።