ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕክምና ፡ ቁመት ለመጨመር ምን አይነት ቀዶ ሕክምና ነው የሚደረገው?
ሳም ቤከር የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ የክፍሉ ረዥም ልጅ ነበር።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነው ጓደኞቹ ሁሉ ዘለግ ዘለግ ያሉ ሲሆኑ የእሱ ቁመት ግን አልጨመረም።
"ኮሌጅ ስገባ ከሌሎች ወንዶችና ሴቶች ያጠርኩ መሆኔን አስተዋልኩ። ሴቶች ከእነሱ ከሚያጥር ሰው ጋር ፍቅር አይጀምሩም። እናም ሚስት አላገኝም ብዬ እሰጋ ነበር" ይላል።
የ30 ዓመቱ የኒው ዮርክ ነዋሪ ሳም እረዝማለሁ ብሎ ቢጠብቅም ቁመቱ አልጨምር አለው።
"ቁመትና ስኬትን አስተሳስሬ ነው የማየው" የሚለው ሳም ቁመት ለመጨመር አማራጮች ያስስ ጀመር።
ከፍ ያለ ጫማ ማድረግ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ወዘተ. . . የሚሉት አማራጮች አላሳመኑትም።
እግር ስለሚያረዝም ቀዶ ሕክምና ሲያነብ ግን ትኩረቱን ሳበው።
"ጥቂት ኢንቾች ከጨመርኩ በኋላ መራመድና መሮጥ እችል ይሆን? ብዬ አሰብኩ"
በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቁመታቸውን ለመጨመር ቀዶ ሕክምና ያደርጋሉ። ቀዶ ሕክምናው ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሳም ስለ ቀዶ ሕክምናው ከእናቱ ጋር ከተወያየ በኋላ የጎንዮሽ ጉዳት ቢኖርም እንኳን ለማካሄድ ወሰነ።
ቀዶ ሕክምናውን ያደረገው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ሲሆን፤ ይህም ከ162 ሴንቲ ሜትር ወደ 170 ሴንቲ ሜትር ከፍ እንዲል አስችሎታል።
"ሐኪሙ መጀመሪያ ሲያገኘኝ ቀዶ ሕክምናው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ነግሮኛል። ጥቂት ኢንቾች ከጨመርኩ በኋላ መራመድና መሮጥ እችል ይሆን? ብዬ አሰብኩ።"
ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሆስፒታል ውስጥ የማገገሚያ ሕክምና ተደርጎለታል። ለስድስት ወራት፣ በሳምንት ለአራት ቀን ሕክምና ይሰጠው እንደነበር ያስታውሳል።
"እንደ አዲስ መራመድ መማር ነበረብኝ" ይላል።
ብዙ አገሮች እግር ለማርዘም ቀዶ ሕክምና ይሰጣሉ። እስከ አምስት ኢንች ወይም 13 ሴንቲ ሜትር ድረስ ቁመት መጨመርም ይቻላል።
አሜሪካ፣ ጀርመን እና ደቡብ ኮርያ የሚገኙ ሆስፒታሎች በዓመት ከ100 እስከ 200 ቀዶ ሕክምናዎችን ያደርጋሉ።
ስፔን፣ ሕንድ፣ ቱርክ እና ጣልያን ውስጥ በዓመት ከ20 እስከ 40 የሚደርሱ ቀዶ ሕክምናዎች ይካሄዳሉ። ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ደግሞ በዓመት 15 ጊዜ ቀዶ ሕክምናው ይደረጋል።
ቀዶ ሕክምናውን የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ቀዶ ሕክምናው እንዴት ይካሄዳል?
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ቀዶ ሕክምናው እስከ 50 ሺህ ፓውንድ ያስከፍላል። አሜሪካ ውስጥ ደግሞ ከ75 ሺህ እስከ 280 ሺህ ዶላር ያስወጣል።
ቀዶ ሕክምናው ውድ ነው። ረዥም ሰዓታት ይወስዳል። ያማልም።
በሕክምናው ፈር ቀዳጅ የሆኑት የሶቪየቱ ጋቪል ሊዝሮቭ ናቸው። ሕክምናውን የጀመሩት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተረፉ ወታደሮችን ለማከም ነበር።
ቀዶ ሕክምናው ባለፉት 70 ዓመታት ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል።
ሕክምናው የሚካሄደው የእግር አጥንትን ቦርቡሮ ለሁለት ከከፈሉ በኋላ አነስተኛ ብረት በክፍተቱ በመክተት ነው።
ግለሰቡ የሚፈለገው ርዝመት ላይ እስኪደርስ ብረቱ በየቀኑ አንድ ሚሊ ሜትር ከፍ እንዲል ይደረጋል።
ታካሚው ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ለወራት የማገገሚያ ሕክምና ይሰጠዋል።
ቀዶ ሕክምናው ነርቭ ሊጎዳ፣ የደም ዝውውር ሊገታም ይችላል። የእግር አጥንትን መልሶ ለመግጠም የሚያስቸግርበትም ጊዜ አለ።
"ቀዶ ሕክምናውን ያደረግኩት በ46 ዓመቴ ነበር"
ባርኒ ቀዶ ሕክምናውን ያደረገው ከአምስት ዓመት በፊት ጣልያን ሲሆን፤ 3 ኢንች ጨምሯል። የእግር ቀዶ ሕክምና እንዲያደርግ የታዘዘው በሐኪሞች ምክር ነበር።
"ቀዶ ሕክምናውን ያደረግኩት በ46 ዓመቴ ነበር። የእግሬ አጥንት መልሶ ሊገጥም አልቻለም። የሦስት ኢንች ክፍተት ተፈጥሮ ነበር" ይላል።
ቀዶ ሕክምናው ምቾት ነስቶት እንደነበር ይናገራል።
"እያንዳንዱ የእግሬ ነርቭ እንደተወጠረ ይሰማኝ ነበር። ህመሙ ቀላል አልነበረም።"
የብሪትሽ የአጥንት ሕክምና [ኦርቶፒዲክ] ማኅበሩ ፕሮፌሰር ሀሚሽ ሲምሰን እንደሚሉት፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሕክምናው እየተሻሻለ መጥቷል።
"ሂደቱ አስተማማኝ እየሆነ ቢመጣም ከአጥንት በተጨማሪ ጡንቻ፣ ነርቭ፣ የደም መዘዋወሪያ እና ቆዳን ማሳደግም ስለሚያስፈልግ ሂደቱ ውስስብ ነው" ይላሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚሠሩት ዶ/ር ዴቪድ ጎደር፤ አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ ለማዳን ብለው ደኅንነቱ በማያስተማምን ቦታ ቀዶ ሕክምናውን እንደሚያገኙ ይናገራሉ።
ባርኒ ቀዶ ሕክምናውን ካካሄደ ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው የመጨረሻውን የሕክምና ደረጃ ያጠናቀቀው። በስተመጨረሻ እግሩ ውስጥ የቀረው ብረት እንዲወጣ ተደርጓል።
"የአንዳንዶች ቀዶ ሕክምና በስኬት ይጠናቀቃል። እኔ ግን ለማገገም ገና ጊዜ ይወስድብኛል። ሆኖም ቀዶ ሕክምናውን ማድረጌ አይጸጽተኝም። አጭር ሰዎች ከሚገጥማቸው መድልዎ ነጻ ሆኜ ሕይወቴን እንድገፋ እድል ሰጥቶኛል" ይላል።