የትራምፕ የጉዞ ገደብ: "በመጨረሻም ልጆቼን ላያቸው ነው"

በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ዘመን አወዛጋቢ ከሚባሉ ውሳኔዎች መካከል ለአሜሪካ የደኅንነት ስጋት በሚል ከተወሰኑ አገራት የሚመጡ ሰዎችን ጉዞ ማገድ ነው።

በበርካቶች ዘንድ ቢወገዝም አሻፈረኝ ያሉትን የዶናልድ ትራምፕን መንበር በቅርቡ የሚረከቡት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የመጀመሪያ የሚቀለብሱት ፖሊሲም እንደሆነ ቃል ገብተዋል።

13 አገራት ላይ ተግባራዊ የሆነው የጉዞ እግድ በተደጋጋሚ የፍርድ ሙግቶች ቢቀርቡበትም እስካሁን ዘልቋል። ለአንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ የዓመታት መለያየት መከራን ሰንቋል።

'የልጄ አምስተኛ መት ልደት ትናንት ተከበረ። ሙሉ ህይወቱን ተለያይተን ነው የኖርነው"

አፈቃብ ሁሴን ሶማሊያዊ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ነው። ለዓመታትም ከልጁም ሆነ ከባለቤቱ ጋር ተለያይቶ ነው ኑሮውን እየገፋ ያለው።

ወደ አሜሪካ፣ ኦሃዮ በጎሮጎሳውያኑ 2015 ሲመጣ፣ በቀጣዩ ዓመት ነፍሰ ጡር ባለቤቱ ወደ አሜሪካ እንደምትመጣ አቅደው ነበር።

ባለቤቱና ልጆቹ ነዋሪነታቸው በኬንያ ቢሆንም ዜግነታቸው ግን ሶማሊያዊ ነው።

የጉዞ እግዱ መጀመሪያ ከተጣለባቸው አገራት መካከል ሶማሊያ የመጀመሪያዋ አገር ናት።

አሜሪካ ከመጣም በኋላ ቤተሰቡን ለማየት የተወሰኑ ጉዞዎች ቢያደርግም መቆየት የቻለው ለአጫጭር ጊዜያት ብቻ ነው።

ይባስ ብሎም ሁለቱ ህፃናት ልጆቹ ሲወለዱም ከባለቤቱ ጎን አልነበረም።

"የባለፉት ዓመታት በህይወቴ ፈታኝ የምለው ጊዜ ነው የገጠመኝ። በጣም ፈታኝ ነው" የሚለው አፈቃብ "መቼም ቢሆን ያለፉትን አራት ዓመታት አልረሳቸውም" ይላል።

ከባድ መኪና ማሽከርከር እንዲህ ቀላል አይደለም፣ ረዥም ሰዓት መስራትና ብቻ መሆንን ይጠይቃል።

በ40 የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥም ነው የሚያሽከረክረው። ባለቤቱን በቻለው መጠን በስልክ ያዋራታል ሆኖም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የስምንት ሰዓታት ልዩነት ፈታኝ አድርጎታል።

እሱ ከሥራው እፎይታ አግኝቶ ሰላም ለማለት ቢደውልም አብዛኛው ጊዜውን ተኝተው ነው የሚያገኛቸው።

በልጆቹ ህይወት ውስጥ ወሳኝ የሚባሉ ምዕራፎች አምልጠውታል "ትናንትና የአንደኛው ልጄ አምስተኛ ዓመት የልደት ቀን ነበር፤ እናም አብሬው አልነበርኩም" በማለት በሐዘን በተሰበረ ልቡ ይናገራል።

አፈቃብ ፈታኝ የሚባሉ ጊዜዎችን ቢያሳልፍም ጆ ባይደን በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ስልጣን በያዙ በመቶ ቀናት ውስጥ ገደቡን አነሳዋለሁ በማለት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ መጪውን በተስፋ እንዲያይ አድርጎታል።

በካሊፎርኒያ የቪዛ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጠበቃ የሆነው አሊ ቦሉር ገደቡ እንደሚነሳና የተለያዩ ቤተሰቦችም እንደገና እንደሚገናኙ ተስፋ ቢኖረውም፤ ከጉዞ እግዱም በፊት ቢሆን እንደ አፈቃብ ያሉ ሙስሊም ወጣቶችን የአሜሪካ የቪዛ ሥርዓት መድልዎ ይፈፅማባቸዋል ይላል።

"ከትራምፕ በፊትም በባራክ ኦባማ ዘመን ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ችግር ነበር" ይላል አሊ።

"ዋናውን ይቅርና በአሜሪካ ያሉ ስደተኞች፣ የስደተኞች ተብሎ የሚጠራውን ቪዛ ለማግኘት ወደ ቆንስላው የሚያመሩ ግለሰቦች እንኳን ሙስሊም መሆናቸው ከታወቀ የኋላ ታሪካቸው መጠናት አለበት በሚል ዓመታትን ይወስዳል። በተለይም ወንዶችና የሆነ እድሜ መካከል ካሉና የመጡትም እነሱ ከማይቀበሏቸው አገራት ከሆኑ ችግሩ የበለጠ ይወሳሰባል" ይላል።

"ዶናልድ ትራምፕ ያደረገው ነገር ቢኖር ከዚህ ቀደም የኦባማም ሆነ ሌሎች መንግሥታት ሲከተሉት የነበረውን ጉዳይ በማጠናከር የጉዞ እግድ በማለት በፖሊሲ ደረጃ ማውጣቱ ነው" በማለት ያስረዳል።

አንዳንዶች የጉዞ እገዳው ሽብርን በመዋጋት ደረጃ አመርቂ ውጤት አምጥቷል ቢሉም ለተለያዩ ቤተሰቦች ግን የማያቋርጥ ቅዠት ሆኖባቸዋል።

"እናቴ አጠገቤ እንደማትሆንና- እንዲህ አይነት ነገር እንደሚፈጠር ባውቅ ኖሮ ልጅ አልወልድም ነበር"

ሚና ማህዳቪ፣ ከካምፕቤል ካሊፎርኒያ ብትሆንም ኢራናዊ እናቷ ወደ አሜሪካ መምጣት አልቻሉም። የልጅ ልጃቸውንም ለማየትና 'እንኳን አይንሽን በአይንሽ አሳየሽ' ለማለትም አልታደሉም።

የመጀመሪያ ልጇን ነፍሰጡር በነበረችበት በ2016 ሚና ለእናቷ በቱሪስት ቪዛ ከኢራን እንዲመጡ አመለከተች።

ልጇን ለመውለድም ሆነ እንዲያርሷትም ስለፈለገች የእናቷን ድጋፍ አጥብቃም ትሻ ነበር። ቪዛውን ባመለከተች በአንድ ወርም ውስጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አብዛኛው ሙስሊም የሕዝብ ቁጥር ያላቸው አምስት አገራት ላይ በፍፁማዊ ትዕዛዝ ገደብ ጣሉ።

ከእነዚህም አገራት መካከል አንዷ ኢራን ናት።

"ዜናውን ልክ ስንሰማ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጆሯችንን ማመን አልቻልንም። ኧረ በጭራሽ አይሆንም፤ አይፈጠርምም አልን። እኔ በአሜሪካ ሕጋዊ ዜጋ ነኝ እሷም የምትመጣው በቱሪስት ቪዛ ነው ብዬ ተረጋጋሁ።"

ነገር ግን እንዳሰበችው አልሆነም የቪዛ ሂደቱ እየተጓተተ መጣ ልጇም ተወለደ፣ "በጣም ከባድ ወቅት ነው" ትላለች።

ምንም እንኳን የቪዛው ሂደት የተጀመረው እግዱ ከመታወጁ ቀድሞ ቢሆንም መልስ ለመስጠት አንድ ዓመት ወስዷል። ከዚያም በኋላም ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ አሜሪካ መግባት እንደማይችሉ ተነገራቸው።

አሁን ልጇ ሦስት ዓመት ተኩል ሆኖታል እስካሁንም ድረስ እናቷ መምጣት አልቻሉም።

ልጇን ያለ እናቷ ማሳደጓ ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜት፣ ጭንቀትና ድብርትም ውስጥ ከቷታል።

"ልጄን በመውለዴ ደስተኛ ነኝ። ነገር ግን እውነቱን ንገሪኝ ካላችሁኝ እናቴ እንደማትመጣ ባውቅ ኖሮ ልጅ በጭራሽ አልወልድም ነበር" ትላለች።

አላስችልም ብሏት አጠር ላለ ቆይታ ወደ ኢራንም ሄዳ ነበር። ከካሊፎርኒያ ኢራን ድረስ ያለው ርቀት ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ በረዥሙ በረራ ወቅት ልጇ እንዳለቀሰና እንደተነጫነጨ ነበር የደረሰው።

እናቷ አሜሪካ መጥተው ከእሷም ጋር ቢቆዩ ምን ያህል ደስታ እንደሚሰማት ብታውቅም "ያንን ድጋፍ እንደማላገኘው ራሴን ማሳመን አለብኝ፤ ወላጆቼ እንደፈለግኩት ሊመጡና ሊመለሱ አይችሉም" በማለትም ታስረዳለች።

ምንም እንኳን የጉዞ እግዱ በተዘረዘሩት አገራት ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ቢሆንም አንዳንዶች ግን ውሳኔው የሚቀለበስበትን መብታቸውን ማስከበር ችለዋል።

የሚና እናት ግን ውሳኔው የሚቀለበስበት ቦታም አልተሰጣቸውም። በካውንስል ፎር አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ በተባለው ድርጅት የስደተኞች መብት ጠበቃ ብሪትኒ ሬዛይ እንደሚሉት ለደንበኞቻው ውሳኔውን ማስቀልበስ ከፍተኛ ፈተና ሆኖባቸዋል።

"መንግሥት በየትኞቹ ሁኔታ ነው ውሳኔ መቀልበስ የሚቻለው የሚለው ላይ ግልፅ ያለ መመሪያ አላወጣም። እናም እኛም ለደንበኞቻችን ሂደቱንንና መመሪያውን በተመለከተ ማስረዳት አልቻልንም" ይላሉ።

ሚና እናቷ አሜሪካ እንዲመጡ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ቢጨንቃት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ጉዳዩን ወስዳው ነበር ነገር ግን እግዱ እስከ 2025 ሊቆይ እንደሚችል አረዷት።

"ልጄ ስምንት ዓመት እስኪሆነው አያቱን በቃ ላያይ ነው? እያልኩ በጣም እያዘንኩ ነበር" የምትለው ሚና የባይደንን መምጣት ተከትሎም እናቷ አሜሪካ መጥተው የልጅ ልጃቸውን በየቀኑ የማቀፍ እድል ይኖራቸዋል የሚልም ብሩህ ተስፋን ሰንቃለች።

'ልጄከባህሉ በፍፁም ተነጥሏል'

ጉልናራ ኒያዝ በቦስተን ተቀማጭነቷን ያደረገች የፎቶ ባለሙያ ናት።

ልጇ ስር መሰረቱንና ባህሉን እንዲረዳ ቤተሰቦቿ አጠገቧ መኖር ነበረባቸው ትላለች። የጉልናራ ቤተሰቦች ትውልዳቸውም ሆነ መኖሪያቸው በማዕከላዊዋ እስያ ኪርጊስታን ነው።

ኪርጊስታን ከጉዞ ገደቡ ዝርዝር የተካተተችው ባለፈው ዓመት ጥር ወር ነበር። የጉዞ ገደቡ በከፍኛ ሁኔታ ያበሳጫት ጉልናራ ልጇ ከወላጆቿ ባህሉንና አመጣጡን እንዳይማርም ደንቃራ ሆኖበታል ትላለች።

"ከባህላችን ፍፁም ተነጥሏል። ገና ታዳጊ በነበረበት 12 ወይም 13 ዓመት እድሜ ላይ እያለ ማማ እንደ አንቺ አይነት አስተዳደግ ያለው እናት እንዴት ከባድ እንደሆነ አትረጂም። አንቺ እኮ ትለያለሽ እንደ ሌሎቹ አይነት እናት አይደለሽም ይለኝ ነበር" ትላለች ጉልናራ።

ጉልናራ ተወልዳ ያደገችው በገጠራዋማ ኪርጊስታን ሲሆን ያደገችበትም ማኅበረሰብ አንድ ቦታ ሰፍሮ የመኖር ሳይሆን ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚኖሩ ናቸው።

ከአስተዳደጓም ጋር ሆነ ከባህሏ ጋር ፅኑ ቁርኝት ያላት ጉልናራ በቦስተንም ይህንኑ የሙጥኝ ብላ ይዛለች። በተለይም ምግብ ላይ ሲመጣ አትደራደርም። የራሷን ሽንኩርት ስታበቅል ሲያይ ልጇ ይደንቀዋል።

"ስለ ባህላችን ቢማር በጣም ጥሩ ነው። ወይ የሩሲያ ቋንቋን ወይም የአፍ መፍቻ ቋንቋችን የሆነውን ኪርጊዝን ቢማር ጥሩ ነው" በማለት ትናገራለች።

ቤተሰቦቿ ወደ አሜሪካ ቢመጡና ለተወሰኑ ወራትም አብረዋቸው ቢቆዩ ከማንነቱና ከባህሉ ጋር ቁርኝት እንዲፈጥር ያረጉት ነበር ነገር ግን የጉዞ ገደቡ ኑሯቸውን ትግል አድርጎባቸዋል።

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ትራምፕ የጉዞ ገደብ

  • ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በዋናነት ይዘው የመጡት ጉዳይ ቢኖር ስደተኞች ላይ ጥብቅ የሆነ ሕግ እንደሚያወጡ በተደጋጋሚ በመናገር ነው።
  • በአንድ ወቅትም "ሙስሊሞችን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ አደርጋለሁ" በማለትም አሜሪካንን ከሽብርተኝነት መከላከል የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው ሲሉም ተናግረው ነበር።
  • የጉዞ ገደቡን ባወጁበትም ወቅት በመላው አሜሪካ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር፤ ተደጋጋሚም ክሶችም ነበሩ።
  • ተችዎች ሕጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሙስሊም አገራት ላይ ገደብ መጣሉ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለው ቢተቹም ዋይት ሐውስ በበኩሉ እርምጃው ያተኮረው ሙስሊሞች ላይ አይደለም በማለትም አስተባብሏል።
  • ከዚህም በተጨማሪም ዝርዝሩ ውስጥ የገቡ አገራት የተመረጡበትን ምክንያቶች በተመለከተ ግልፅ በሆነ መንገድም አልተነገረም።