ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቦረና አባ ገዳ ኦነግ-ሸኔ የሕዝብ 'ጠላት ነው' ሲሉ አወጁ
የቦረና አባ ገዳ የሆኑት ኩራ ጃርሶ በምዕራብና በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሽምቅ ጥቃት እየፈጸመ እንደሆነ የሚነገረውን ኦነግ-ሸኔን የሕዝብ ጠላት ነው ሲሉ ቡድኑን አወገዙ።
አባ ገዳ ኩራ ለቢቢሲ እንደረናገሩት በታጣቂ ቡድኑ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሠላማዊ ሰዎች በመገደላቸው በመሆኑ ነው። "እነዚህ ታጣቂዎች የቦረናን ሕዝብ እየገደሉ ነው። ለሕዝብ እታገላለሁ የሚል አካል መልሶ ሕዝብን መግደል የለበትም" ሲሉ ነው ቡድኑን ያወገዙት።
ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተነጥሎ የወጣው ታጣቂው የኦነግ-ሸኔ ቡድን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ጥቃት እንደፈጸመና መንግሥትም ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ መግለጹ አይዘነጋም።
የቦረና አባ ገዳው ኩራ ጃርሶ የኦነግ-ሸኔ አባላት እንዳሉት "ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ። በቦረና ባህል ይህ እጅግ አጸያፊ ነው። ባል እያባረሩ ከሚስት ጋር ያድራሉ። የጦር መሣሪያ ይነጥቃሉ። ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ይገድላሉ። ከብት ዘርፈው አርደው ይበላሉ" ሲሉ ቡድኑ እየደረሰ ነው ያሉትን ድርጊት ገልጸዋል።
ቡድኑ በምዕራብና በደቡብ የተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ እንዲሁም በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር በተደጋጋሚ ሲዘገብ ነበር።
አባ ገዳ ኩራ እንዳሉትም የቡድኑ አባላት በእድሜ የገፉ አዛውንቶችን እና ሕጻናትን ጨምር እየገደሉ መሆኑን በመግለጽ ለዚሁ መሳያ የሚሆን ምሳሌም ጠቅሰዋል።
"ለምሳሌ አሬሮ ወረዳ የ12 ዓመት ልጅ ገድለዋል" ያሉት አባ ገዳው አያይዘውም "እዚህ ደረጃ ላይ ስለደረሱ ኦነግ-ሸኔ የቦረና ሕዝብ ጠላት ነው ብለን አውጀናል። ሕዝቡ ራሱን እንዲከላከል አውጀናል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጭምር ወደ አገር እንዲገቡ ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም ከገቡ ጀምሮ ችግር ሆነው መቆየታቸውን አባ ገዳ ኩራ ተናግረዋል።
"በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ አባ ገዳዎች እና የቦረና ሽማግሌዎች ሁሉ ለምነን አቅቶናል። አላማቸው ምን እንደሆነ ሊገባን አልቻለም" ሲሉም ተናግረዋል።
ኦነግ ሸኔ የሕዝብ ጠላት ነው ብለው ያወጁት በሕዝቡ ላይ ጉዳት በማድረሳቸው እንጂ በማንም ጫና ምክንያት እንዳልሆነ አስረግጠው፤ "አሁን ሕዝቡ በሁሉም ቀበሌዎች ታጣቂዎቹን እየወጋ ነው" ብለዋል።
የቦረና አባ ገዳ ባማኅበረሰባቸው ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሲሆኑ የሚያስተላልፉትም መልዕክት የተነሳ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥት ዘንድም ተሰሚነት አላቸው።
መንግሥትም የተለያዩ መልዕክቶችን ወደ ኅብረተሰቡ ማስተላለፍ ሲፈልግም በአባ ገዳዎች አማካይነት የሚያደርስበት አጋጣሚዎችም አሉ።
መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች፣ በወለጋ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ በሚገኙት ጉጂ እና ቦረና ዞኖች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች በአካባቢዎቹ የሚንቀሳቀሱትን የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።
ቡድኑንም ከምዕራብና ከደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ለማስወገድ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አካላት በተለያዩ ጊዜያት ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።