ኦነግ-ሸኔ፡ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው አለ

የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተነጥሎ እንደወጣ በሚነገርለትና ኦነግ-ሸኔ ተብሎ በሚታወቀው ታጣቂ ቡድን ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተነገረ።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው የክልሉ ልዩ ኃይል ከሰሞኑ በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ባካሄደው ዘመቻ በታጠቂው ቡድን አባላት ላይ "ድል" ተመዝግቧል ብሏል።

በዚህም በደቡብ ኦሮሚያ በሚገኘው የጉጂ ዞን 14 የኦነግ-ሸኔ አባላት መገደላቸውን የዞኑን አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶን ጠቅሶ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ኦሮሚያ አንዳንድ ስፍራዎች የቴሌኮም አገልግሎቶች ከተቋረጡ አራት ቀናት ማለፋቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቴሌኮም አገልግሎቶቹ እንዲቋረጡ ተደረገው የክልሉ መንግሥት በተለያዩ ስፍራዎች በታጣቂዎች ላይ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች በሚገኙ እንደ ደምቢ ዶሎ፣ ቤጊ እና ጊዳሚ ከተሞች ስልክ እንደማይሰራ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።

መቀመጫቸውን ነቀምቴ ከተማ ያደረጉት የኢትዮቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙላቱ ጋዲሳ ከላይ በተጠቀሱት ስፍራዎች የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጣቸው የተሰማው ከጥቅምት 25 ጀምሮ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን በአካባቢዎቹ የቴሌኮም አገልግሎቱ ለምን እንደተቋረጡ እንደማያውቁ አቶ ሙላቱ ገልጸዋል።

"አገልግሎቱን ለማቋረጥ እና ለማስጀመር ስልጣኑ አልተሰጠንም። የእኛ ኃላፊነት ለደንበኞች አገልግሎት መስጠት ነው" ብለዋል።

የሞባይል ስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ለኢትዮቴሎኮም የበላይ አስተዳደር አስታውቀው ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በምዕራብ ኦሮሚያ ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ላይ መንግሥት እርምጃ በወሰደበት ጊዜ የቴሌኮም አገልግሎት ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ እንዲቆይ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የጦር ክንፍ ነው የሚለው የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምዕራብ ኦሮሚያ እና በጉጂ ዞኖች እንደሚንቀሳቀሱ የሚነገር ሲሆን በስፍራዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የክልሉ መንግሥት ቡድኑን ተጠያቂ ያደርጋል።

ቡድን በክልሉ በንጹሃን ዜጎች እና በአካባቢ ባለስልጣናት ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያዎች ጋር በተደጋጋሚ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል።

በቅርቡም በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ በተበላው አካባቢ ለተገደሉት 36 ሰዎች የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ተጠያቂ መሆናቸው ተነግሯል።