ትግራይ፡ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኃላፊነታቸው ተነሱ

አህመድ ኢሴ አዋድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከኃላፊነታቸው የተነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አህመድ ኢሴ አዋድ

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሁሴይን ሮብሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ የሶማሊያ አቋም ውዝግብ ማስነሳቱን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን አህመድ ኢሴ አዋድን ከኃላፊነታቸው አንስተዋቸዋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን አንድነት እንደግፋለን የሚል መልዕክት በመስሪያ ቤቱ ይፋዊ ትዊተር ገፁ ወጥቷል።

"የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአገሪቷን ግዛት ለማስከበር በሚያደርጉት እርምጃ ሶማሊያ ያላትን ድጋፍ እንደገና ታረጋግጣለች" የሚል መግለጫ በመስሪያ ቤቱ ትዊተር ገፅ ቢወጣም ከሰዓታት በኋላ መልዕክቱ ተነስቷል።

በትናንትናው ዕለትም አህመድ ኢሴ አዋድ በግላቸው የትዊተር ገፅ "ሶማሊያ በኢትዮጵያ ስለተፈጠረው ግጭት ምንም አይነት ይፋዊ መግለጫ አልሰጠችም" በማለትም አስተባብለዋል።

ይህንንም ውዝግብ ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን በሳቸውም ቦታ መሃመድ አብዲሪዛክ መሃመድ አብዱቃድር እንደተተኩም ከሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከኃላፊነታቸው የተነሱት ሚኒስትርም አምባሳደር ተደርገው እንደተሾሙም የአገሪቷ የመንግሥት ሬድዮ ድረገፅ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ሆኖም አህመድ ኢሴ አዋድ በአሁኑ ወቅት "በአምባሳደርነትም ሆነ በየትኛውም ቦታ ለመሾም ዝግጁ እንዳልሆኑ" በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ይፋዊ የትዊተር ገፅም ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ ቢገልፅም ምክንያቱ አልተጠቀሰም።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የትግራይ ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘውን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ወታደራዊ ግጭት መቀስቀሱን አስታውቀዋል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጦርነቱ ውስንና በተወሰኑ የህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረና ሕገ መንግሥትን ለማስከበር እየተወሰደ እርምጃ መሆኑን ገልፀው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ መግለፃቸው ይታወሳል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጦርነት እንደተከፈተበትና ሕዝቡም ላይ ያነጣጠረ ነው ይላል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ስር ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታለች።

በባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ 3 ሺህ ወታደሮቿንም እንዳስወጣች የሶማሊያው ዳልሳን ሬድዮ ዘግቦ ነበር።