ኮሮናቫይረስ ፡ ስንት ተስፋ ሰጪ የኮቪድ-19 ክትባቶች ተገኝተዋል?

የተለያዩ ተቋሞች የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት መቃረባቸውን እያስታወቁ ነው። ይህም ለመላው ዓለም ተስፋ የሰጠ ዜና ሆኗል።

ከሳምንት በፊት ፋይዘር እና ባዮቴክ የተባሉ ተቋሞች ውጤታማነቱ አስተማማኝ የሆነ ክትባት ማግኘታቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።

አሁን ደግሞ ሞዴርና የተባለ ድርጅት ውጤታማ የኮቪድ-19 ክትባት ሙከራ ማድረጉን ይፋ አድርጓል።

በኦክስፎርድ የሚካሄደው የክትባት ምርምር በ60ዎቹ እና 70ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ላይ በሽታ የመከላከል አቅምን ከማዳበር አንጻር ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል።

ሌለው በክትባት ምርምር ውጤታማ እየሆነ የሚገኘው የቤልጄሙ ጃንሰን ሲሆን፤ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሦስተኛ ደረጃ ሙከራ ላይ ይገኛል።

ክትባት ሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም እንዲያዳብር በማገዝ፤ ሕይወት ወደቀደመው ገጽታ እንዲመለስ ይረዳል።

ሰዎች በወረርሽኙ እንዳይያዙም ያግዛል። ወይም ደግሞ የበሽታውን አደገኛንት ይቀንሳል።

ክትባቶቹ ምን ልዩነት አላቸው?

ክትባት የሚሠራው ሰውነት በሽታውን የሚከላከልበትን አቅም ለማዳበር ሲሆን፤ ሰውነት ቫይረሱ እንግዳና አደገኛ እንደሆነ ተገንዝቦ እንዲዋጋ ያግዛል።

ፋይዘር እና ባዮቴክ እንዲሁም ሞዴርና ያገኙት አርኤንኤ የተባለ ክትባት ነው።

ይህም የቫይረሱን የዘረ መል ቅንጣቶች ሰውነት ውስጥ በመክተት፤ ሰውነት በሽታውን ለይቶ የመከላከል አቅም እንዲያዳብር የሚደረግበት መንገድ ነው።

በጃንሰን የሚሠራው ክትባት ደግሞ ዘረ መሉ የተሻሻለ የጉንፋን ቫይረስን በመጠቀም፣ ኮሮናቫይረስን እንዲመስል አድርጎ ጎጂነቱን ለመቀነስ ይሞክራል።

በዚህ መንገድ ሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም አዳብሮ ወረርሽኙን እንዲከላከል ይደረጋል።

በኦክስፎር እና በሩስያ የሚሠሩት ክትባቶች ጉዳት አልባ ቫይረስን ዝንጀሮ ላይ ይሞክራሉ። ከዚያም ዘረ መሉን አሻሽሎ ከኮሮናቫይረስ ጋር እንዲመሳሰል በማድረግ ውጤት ለማግኘት ይሞከራል።

በቻይና የተሠሩት ሁለት ክትባቶች የተጠቀሙት ራሱን ቫይረሱን ነው። ቫይረሱ ጉዳት እንዳያስከትል ካከሰሙት በኋላ ነው ምርምሩ የተሠራው።

ሰዎችን ለቫይረሱ በማጋለጥ የሚሠሩ ምርምሮች የትኛው ክትባት የተሻለ ውጤታማ እንደሆነ ለመረዳት ያግዛሉ።

ክትባት መቼ እናገኛለን?

ፋይዘር በዚህ ዓመት መጨረሻ 50 ሚሊዮን ጠብታዎችን በመላው ዓለም እንደሚያከፋፍል ተናግሯል። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 1.3 ቢሊዮን ጠብታዎች ይገኛሉ።

ለምሳሌ ዩናይትድ ኪንደም በዓመቱ መጨረሻ 10 ሚሊዮን የክትባት ጠብታ እንደምታገኝ ይጠበቃል። ተጨማሪ 30 ሚሊዮን ክትባቶች ማዘዟንም አስታውቃለች።

ሌለው ጥያቄ ክትባቱን በቅድሚያ ማን ያገኛል? የሚለው ነው።

ይህ የሚወሰነው ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ በሚሰራጭባቸው እና የበለጠ ውጤታማ በሆነባቸው አካባቢዎች ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም በቅድሚያ ክትባቱን የምትሰጠው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ለሆኑት በእድሜ የገፉ ሰዎችና እንክብካቤ ሰጪዎቻቸው ነው።

ክትባቱ ውጤታማ መሆኑ የሚታወቀው ሁሉም የሙከራ ደረጃዎች ታልፈው ክትባቱ በሽታን እንደሚከላከል ወይም በበሽታው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንደሚቀንስ ሲታወቅ ነው።

ክትባቶች ፍቃድ አግኝተው፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ጠብታዎች መመረትም አለባቸው።

ቫይረሱን ከምድር ላይ ለማስወገድ ከ60 እስከ 70 የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በሽታውን የመካከል አቅም ማዳበር አለበት።