ብራዚል ተስፋ ያደረገችበት ቻይና ሰራሹ የኮቪድ ክትባት “በአስቸኳይ ይቁም” አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብራዚል ትልቅ ተስፋ አሳድራበት የነበረው ቻይና ሰራሽ የኮቪድ ክትባት እንዲቆም አዘዘች። ምክንያቱ ደግሞ “ጠጠር ያለ የጎንዮሽ ጉዳት” በማስከተሉ ነው።
የብራዚል የጤና ቁጥጥር አንቪሳ እንዳለው በተሞከረባቸው ሰዎች ላይ ከበድ ያለ ጉዳት ያስከተለው በኦክቶበር 29 ነው። የቁጥጥር መሥሪያ ቤቱ ደረሰ ያለው የጤና ጉዳት ምን እንደሆነ ግን ከመናገር ተቆጥቧል።
የቻይናው ሲኖቫክ ያመረተው ኮሮናቫክ ክትባት በዓለም ላይ የመጨረሻ ምዕራፍ ሙከራዎች እያደረጉ ከነበሩና ተስፋ ከተጠላባቸው ክትባቶች አንዱ ነበር። ብራዚል ይህ የቻይና ክትባት ይቅርብኝ ትበል እንጂ ቻይና ግን ክትባቱን አገልግሎት ላይ አውለዋለች።
በሺ የሚቆጠሩ ዜጎችን በአስቸኳይ መከላከል እንዲረዳቸው ሰጥቻቸው በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው ብላለች። ቻይና ይህን ክትባት የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋዋ እንዲከተብ ታበረታታለች።
ባለፈው ወር ዩዉ ከተማ ቢቢሲ በቀረጸው አንድ ቪዲዮ ይህንን ከትባት ለመውሰድ የተሰለፉ ሰዎችን ያሳያል። ሲኖቫክ መድኃኒት አምራች ሁሉም ሰራተኞቹ ይህንን ክትባት በቻይና ውስጥ መውሰዳቸውን ይናገራል።
ቢቢሲ አሁን ብራዚል ላይ በዚሁ ክትባት ዙርያ ደረሰ በተባለው ጉዳት ከሲኖቫክ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።ብራዚል በዓለም ላይ ኮሮና መጠነ ሰፊ ጉዳት ካደረሰባቸው አገራት ተርታ ትመደባለች። 5 ሚሊዮን 6መቶ ሺህ ዜጎቿ በተህዋሲው ተጠቅተውባታል።
163ሺ ሰዎች ደግሞ ሞተውባታል።ይህ አሐዝ ብራዚልን ከአሜሪካ እና ከሕንድ ቀጥሎ ሦስተኛዋ ተጎጂ አገር ያደርጋታል።ሙከራው ለምን እንዲቆም ተደረገ?ሰኞ ዕለት የቁጥጥር መሥሪያ ቤቱ ኮሮናቫክ የሙከራ ክትባት እንዲቆም ወሰነ።
ይህም የተስተዋሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ስላሉ ነው በሚል ተገለጸ።ነገር ግን ምን እንደተከሰተም ሆነ የት እንደተከሰተ አልገለጠም። ይህ የሲኖቫክ ክትባት የመጨረሻ ሙከራ ከብራዚል ሌላ በኢንዶኒዚያ እና ቱርክም በሙከራ ላይ ይገኛል።
ነገር ግን ሁለቱ አገሮች እንደ ብራዚል ያለ ተመሳሳይ ቅሬታን አላቀረቡም።ዲማስ ኮቫስ ቡታንታን የተባለው የሕክምና ጥናት ኢንስትዩት ኃላፊ ነው። እሱ እንደሚለው የቻይና ሰራሹ ክትባት እንዲቆም የሆነው ከሞት ጋር በተያያዘ ነው። ሆኖም ግን የተከሰተው ሞት ከክትባቱ ጋር ላይያያዝ ይችላል ብሏል።ሙከራ ላይ ያለ ክትባት በዚህ መንገድ እንዲቆም ማድረግ አዲስ ነገር አይደለም።
ባለፈው ጥር ለምሳሌ የታላቋ ብሪታኒያ ተስፋ የተጣለበት ክትባት የጎንዮሽ ጉዳቶችን አስከትሏል በሚል እንዲቆም ማድረጓ ይታወሳል።ይህ ክትባት ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ከአስትራዜኒካ ጋር በጥምረት እየፈበረከው የሚገኝ ነበር።
ሙከራው እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ግን በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲቀጥል ተደርጓል።የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ጃይል ቦልሴናሮ አገራቸው የቻይና ሰራሽ ክትባት እንደማትጠቀምና ምርጫቸው የኦክስፎርድ ክትባት እንደሆነ በይፋ ተናግረው ያውቃሉ።
በአሁን ሰዓት የቻይናውን ሲኖቫክን ጨምሮ በመላው ዓለም በርከት ያሉ የክትባት ሙከራዎች የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ናቸው። ትናንት በወጣ ሰበር ዜና የአሜሪካው መድኃኒት አምራች ፊዘር እጅግ ውጤታማ የተሰኘ ክትባት ማግኘቱን ይፋ አድርጓል። ይህ ክትባት ፈዋሽነቱ 90 ከመቶ መሆኑ ለዓለም ብስራት ሆኗል።














