ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ አስተዳደር “ምርጫው አልተጠናቀቀም” እያሉ ነው
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቃለ አቀባይ የጆ ባይደን ድል ለመገዳደር የምናካሂደው ሕጋዊ ትግል ገና መጀመሩ ነው አሉ።
“ምርጫው አልተጠናቀቀም። ገና ብዙ ይቀረዋል” ሲሉ የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ኬሊ ማኬኔኒ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ቢከሱም ለዚህ ማስረጃ የሚሆን ግን አላቀረቡም።
ሪፓብሊካኑ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው መሸነፋቸውን አምነው አልተቀበሉም። ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ባሳለፍነው ቅዳሜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ማሸነፋቸው መታወጁን ተከትሎ ስልጣን ከመረከባቸው በፊት ቅድመ ዝግጅቶቻቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን በአንዳንድ ቁልፍ ግዛቶች በምርጫ ውጤት ላይ ሕጋዊ ጥያቄዎችን አነሳለሁ እያሉ ነው። ትናንት ምሽት ላይም በትዊተር ገጻቸው በድምጽ አሰጣጥ ላይ “መገመት የሚከብድ እና ሕገ-ወጥ” ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ትራምፕ ለዚህ ክሳቸው ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም።
የትራምፕ ጠበቆች ተጭበርብሯል የሚሉት ምኑን ነው?
ሰኞ ዕለት በዋይት ሃውስ በነበረው መግለጫ ላይ የትራምፕ አስተዳደር በምርጫው ላይ ማጭበርበር ስላለ የፕሬስ አካላት ጉዳዩን በማጣራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቋል። ፎክስ ኒውስ የዋይት ሃውሱ መግለጫ ማስረጃ አያቀርብም በማለት መግለጫውን አቋርጧል።
የትራምፕ ጠበቆች በቁልፍ ግዛቶች የሚያነሷቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።
ፔንሲልቬኒያ
የትራምፕ ጠበቆች በፔንሲልቬኒያ ግዛት በሚገኙ ግዛቶች የሪፐብሊካን ምርጫ ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መሄድ አለመቻላቸውን በማስመልከት በፌደራል ፍርድ ቤት ክስ መስረተው ነበር።
ጠበቆቹ ፍርድ ቤቱ ባይደን በፔንሲልቬኒያ ግዛት ማሸነፋቸውን እንዳያረጋግጥ የሚጠይቅ ነው። ፍርድ ቤቱ ግን ይህን ክስ ውድቅ አድርጎታል።
ሚሺጋን
ባይደን በዚህ ግዛት እንደሚያሸንፉ ተገምቷል። የትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን በምርጫው ዕለት የሪፐብሊካን ምርጫ ታዛቢዎች ወደ ድምጽ መቁጠሪያ ጣቢያዎች ገብተው መታዘብ አልቻሉም በሚል ምክንያት በሚሺጋን የድምጽ ቆጠራው እንዲቆም ያቀረቡት ጥያቄ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ የትራምፕ ጠበቆች ጥያቄን ውድቅ ያደረጉት በቂ ማስረጃ መቅረብ አልቻሉም በሚል ነው።
ዊስኮንሰን
የትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን በዊስኮንሰን ግዛት ዳግም ቆጠራ እንዲካሄድ እጠይቃለሁ ብሏል። በዊስኮንሰን ግዛት ድምጽ ተቆጥሮ አልተጠናቀቀም፤ በዚህም የጠበቆቹ ጥያቄ መቼ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
ኔቫዳ
የኔቫዳ ሪፐብሊካን ፓርቲ "ከዚህ ቀደም የኔቫዳ ነዋሪ የነበሩ እና አሁን በሌላ ስፍራ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የምርጫ ሕጉን ተላለፈው ድምጽ እንዲሰጡ ተደርጓል" ብሏል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ ጠበቆች ነዋሪነታቸው ኔቫዳ ግዛት ሳይሆን በኔቫዳ ድምጽ የሰጡ የሰዎች ስም ዝርዝርን ይፋ አድርገዋል። ምርጫ አስፈጻሚዎች ግን የተጣሰ የምርጫ ሕግ የለም እያሉ ነው።
አሪዞና
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላት ቅዳሜ ዕለት በሕጋዊ መንገድ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ድምጽ ሰጪዎች ድምጻቸው እንዳይቆጠር ተደርጓል በማለት በአሪዞና ይግባኝ ብለዋል። ይህ የይግባኝ ጉዳይ በፍርድ ቤት እየተመረመረ ይገኛል።