ከተክሎች ጋር መኖርና እነሱን መንከባከብ ለጤናችን ምን ያክል ይጠቅማል?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካቶች አነስተኛ ተክሎችን በቤታቸው ማሳደግና መንከባከብ ጀምረዋል። በተጨማሪም ሰፋ ያለና ምቹ ግቢ ያላቸውም ሰዎች በግቢያቸው ውስጥ ትልልቅ ዛፎችን መትከል እየተለመ መጥቷል።

ለመሆኑ ከተክሎች ጋር መኖርና እነሱን መንከባከብ ለጤናችን ምን ያክል ይጠቅመን ይሆን?

ዛፎች ሕይወትዎን ማዳን ይችላሉ፣ ደስተኛ ያደርጋሉ እንዲሁም ጠንካራ ጭንቅላት እንዲኖርዎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይጫወታሉ የሚል ዓለም አቀፍ ጥናት በቅርቡ ተሰርቶ ነበር።

ምንም እንኳን ዛፎች ጎርፍን፣ ድርቅን እና የአፈር መሸርሸርን ለመካከል ጠቃሚ እንደሆኑ ለብዙ ዓመታት በበርካታ ባለሙያዎች የተጻፈ ቢሆንም ዛፎች ከሰው ልጆች አስተሳሰብና የጭንቅላት አሠራር ጋር ስላላቸው ቁርኝት ግን ብዙም አልተባለም።

ብዙዎቻችን እንደምናስበው ንጹህ አየር እንድንተነፍስ ብቻ ሳይሆን ተክሎች በርካታ ጠቀሜታዎች አሏቸው። ዛፎችንና አረንጓዴ ተክሎችን ዝም ብሎ መመልከት በራሱ ማዕከላዊ የአዕምሮ ክፍላችንን እንደሚያረጋጋው የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ዛፎችን መመልከት በጭንቅላታችን ውስጥ የሚመረተውን ኮርቲሶል የሚባለውን ለጭንቀት እጢ የሚያጋልጥ ንጥረ ነገር መጠን ይቀንሳል፣ የልብ ምትን ዝግ ያደርጋል፣ የደም ግፊትንም ይቀንሳል። ሌላው ቀርቶ የዛፎችን ፎቶ መመልከት እንኳን በጭንቅላታችን ውስጥ ጥሩ ስሜት ይፈጥራል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዓለማችን ከመቼውም በላይ እየሞቀች ነው። እንደ የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ከሆነ፤ በዓለም ዙሪያ ኢንዱስትሪው ከመስፋፋቱ በፊት ከነበረው የአየር ጠባይ ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ሰዓት የዓለማችን ሙቀት በአንድ ዲግሪ ጨምሯል።

በዚህ አካሄድ 2100 ላይ የዓለም ሙቀት ከ3-5 ዲግሪ ሰሊሺየስ የሚጨምር ይሆናል።

ምንም እንኳን በኢንዱስትሪው ዘርፍ የበለጸጉት አገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን በካይ ንጥረ ነገር መቀነስ ወሳኝ ቢሆንም ይህንን የዓለማችንን በከፍተኛ ሁኔታ መሞቅ ለመቀነስና ብሎም ለማስቀረት ተክሎች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

ምናልባት እያንዳንዱ ሰው በቤቱ ውስጥ የሚያስቀምጣቸው አነስተኛ ተክሎች አልያም በአቅራቢያው የሚተክላቸው ዛፎች ለውጥ የሚያመጡ ላይመስል ይችላል፤ ነገር ግን በቢሊየኖች የሚቆጠረው የዓለም ህዝብ ሲደመር ግን ትልቅ ለውጥ ይፈጠራል።

ሌላው ቀርቶ በቤታችን የምናስቀምጣት ትንሿ ተክል በትንሹም ቢሆን ጥቅም አላት። ለአእምሯችን ከምትሰጠው ሰላምና እረፍት በተጨማሪ የምንተነፍሰውንም አየር ጭምር ትቆጣጠራለች።

የዘርፉ ባለሙያዎች የቤት ውስጥ ተክሎች በቤት ውስጥ ያለውን አየር እንዲሻሻልና ሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም ብናኞች፣ አላስፈላጊ ጋዞች እንዲሁም መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድ ይጠቅማሉ።

ከእነዚህ ውስጥ እንደ በለስ፣ የመጥበሻ ቅጠል፣ ብርቱካን፣ ካላንኮ፣ ማሬል የመሳሰሉ እፅዋት ይገኙበታል።

በሆስፒታል ተኝተው የሚገኙ ታማሚዎች በመስኮታቸው በኩል ዛፎችን ማየት ከቻሉ የመዳን ፍጥነታቸው ይጨምራል ይላሉ ባለሙያዎቹ። ዛፎች ያላቸው የማረጋጋት አቅም ጭንቀትንና ህመመን እስከመቀነስ ይደርሳል።

ተፈጥሯዊ በሆኑ ዛፎች መካካል ሥራቸውን የሚያከናውኑ ሠራተኞችም ቢሆን ውጤታማነታቸው ከሌሎች ከፍ ያለ እንደሚሆን ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በአጠቃላይ አንድ የቤት እንስሳ እንደምናሳድገው ሁሉ አንድ ተክል በቤታችን ካለ የምናገኘው ደስታ ወደር የለውም። በተጫማሪም ተክሎቹን በመንከባከብ የምናሳልፈው ጊዜ የሚሰጠን የአእምሮ እርካታ ከፍተኛ ነው።