ዋሺንግተን ሟቾች ወደአፈር እንዲቀየሩ ፈቀደች

ዋሺንግተን የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ ወደአፈርነት እንዲቀየር በመፍቀድ ከአሜሪካ ግዛቶች ቀዳሚ ሆነች።

አዲስ በወጣው ሕግ መሰረት ሰዎች ከሞቱ በኋላ ወደ አፈርነት ለመለወጥ ከፈቀዱ ፍላጎታቸው እውን ይሆናል።

አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ግብአተ መሬቱን መፈፀም አልያም ማቃጠልን እንደሚቻል ሁሉ ይህም እንደ አማራጭ ይታያል። የመቃብር ስፍራ እጥረት ባለባቸው ከተሞችም ተግባራዊ አማራጭ ሆኖ ይቀርባል።

የሟቾች አስክሬን እንዲበሰብስና አፈር እንዲሆን ከተደረገ በኋላ ቤተሰቦች አፈሩን በመውሰድ አበባ ወይም ዛፍ ሊተክሉበት፣ ሰብል ሊያለሙበት ይችላሉ።

ይህ ሕግ የተፈረመው ማክሰኞ እለት ነው።

ካትሪን ስፔድ ይህ ሕግ እንዲፀድቅ ስትወተውት የነበረ ሲሆን፤ ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ የመጀመሪያውን ድርጅት አቋቁማለች።

"የሟቾችን ገላ ወደአፈር መቀየር ከመቅበር፣ ከማቃጠል፣ ይልቅ ተፈጥሯዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ ሲሆን ውጤቱም የካርቦን ልቀትን የሚቀንስና የመሬት አጠቃቀማችንን የሚያስተካክል ነው" ብላለች ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል በላከችው መግለጫ።

የስፔድ ድርጅት የሰውን ገላ ለማፈራረስ በባለስድስት ጎን እቃ ውስጥ ካስቀመጡ በኋላ በአልፋልፋ፣ በእንጨት ስብርባሪና በሳር ይሞሉታል።

ሳጥኑ በሚገባ ከታሸገ በኋላ በ30 ቀን ውስጥ ፍርስርስ ብሎ ሁለት ጋሪ አፈር ይወጣዋል።

በአሁኑ ሰአት አካባቢን የማይጎዱ የቀብር ሥርአቶች እየተበረታቱ ይገኛሉ።

ስዊድን የሰው ልጅን 'አፈር ነህና አፈር ትሆናለህ' በማለት አስቀድማ ሕጉን ያፀደቀች ሲሆን፤ በዩናይትድ ኪንግደም ያለሬሳ ሳጥን ወይንም የአፈርን ተፈጥሮ በማይጎዱ ሌሎች ነገሮች መቀበር በሕግ ፀድቋል።