የአሜሪካ ምርጫ፡ ትራምፕ እና ባይደን የመጨረሻ ሰዓት ቅስቀሳ እያደረጉ ነው

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እሁድ ዕለት የመጨረሻ ቅስቀሳዎቻቸውን ለማካሄድ ወደተለያዩ የአሜሪካ ክፍሎች ተጉዘዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በአገሪቱ የሚገኙ አምስት ጦርነት የተካሄደባቸውን ቦታዎች የጎበኙ ሲሆን፤ ጆ ባይደን ደግሞ ፔንሲልቬኒያ ውስጥ የምረጡኝ ቅስቀሳቸው በማካሄድ ንግግር አድርገዋል።

የዴሞክራቲክ ፓርቲው እጩ ከማክሰኞ በፊት እየወጡ ባሉ መረጃዎች መሰረት በአጠቃላይ ከትራምፕ በተሻለ ድምጽ እያገኙ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።

ነገር ግን ወሳኝ በሚባሉ ግዛቶች ያላቸው ብልጫ እምብዛም ስላልሆነ የምርጫውን ውጤት ሊቀየር ይችላል ተብሏል።

ከ90 ሚሊየን በላይ ሰዎች በፖስታ ከወዲሁ ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን፤ በአገሪቱ ታሪክ በፖስታ ይህን ያክል ቁጥር ያለው ዜጋ ሲመርጥ ይህ ከፍተኛው ነው።

ምናልባት መላው ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ለዚህ ምክንያት እንደሆነም ተገምቷል። አሜሪካ እስካሁን ከየትኛውም የዓለም አገር የሚበልጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አስመዝግባለች።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ብቻ 99 አዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተዘግቧል።

የአሜሪካ ከፍተኛ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የኮሮናቫረስ ስርጭትን በመቆጣጠር ረገድ የወሰደውን እርምጃ የተቹ ሲሆን፤ ዋይት ሀውስ ደግሞ ንግግራቸው ፖለቲካዊ አላማ ያለው ነው ሲል ከሷል።

ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻቸው የመጨረሻዎቹን አምስት ግዛቶች አዳርሰዋል።

ሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንት እሁድ በእጅጉ የተጨናነቀ ጉዟቸውን አድርገዋል። በመጀመሪያ በሎዋ ሰልፈኞችን ያገኙ ሲሆን፤ ሚቺጋን እና ሰሜን ካሮላይናም ሄደዋል። በመቀጠል ጆርጂያ እና ፍሎሪዳ ግዛቶችን አዳርሰዋል።

እነዚህ ሁሉም ግዛቶች በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ከፍተኛ ፉክክር የሚካሄድባቸው ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ በሚቺገን ለሚገኙ ደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲያደርጉ ''በእኔ አመራር የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እያደገ ነው'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ደግሞ አሜሪካውያን ''ከአደገኛ የባይደን የእንቅስቃሴ ገደብና ደህንነቱ ከተጠበቀ ክትባት'' መካከል መምረጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳይ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን መካከል ዋነኛ ከሚባሉት የመከራከሪያ ነጥቦች አንዱ ከሆነ ቆይቷል። ጆ ባይደን ምርጫውን ካሸነፉ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ሊጥሉ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ጠቁመዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ መጣል የአሜሪካን የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ይከተዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

ዴሞክራቱ ባይደን በፊላደልፊያ በነበራቸው ቅስቀሳ ወቅት ለጥቁር አሜሪካውያን ንግግር አድርገዋል።

በአሜሪካ ያለውን ''መዋቅራዊ ዘረኝነት'' እንደሚዋጉ የገለጹ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕን ደግሞ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ ወረፍ አድርገዋቸዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሰጡት ምላሽ በብዙዎች ዘንድ እንዲተቹ አድርጓቸዋል።

ትራምፕ መጋቢት ላይ በወረርሽኙ ምክንያት ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲደነግጉ ተቀባይነታቸው ጨምሮ ነበር። 55 በመቶ አሜሪካውያን በወቅቱ ድምፃቸውን ለእሳቸው ሊሰጡ እንደሚችሉ አንድ ድምፅ ሰብሳቢ ድርጅት አሳውቆ ነበር።

ነገር ግን በቅርቡ የተሰበሰበ አንድ ድምፅ እንደሚጠቁመው የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ጭምር ትራምፕን ፊት ነስተዋቸዋል።

ለዚህም ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጭምብል መልበስን ጨምሮ በወረርሽኙ ላይ ያላቸውን አቋም እያለሳለሱ ያሉት ይላሉ ባለሙያዎች።