ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ አማካሪ አሜሪካ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን መቆጣጠር አትችልም አሉ
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ አገሪቱ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን መቆጣጠር እንደማትችል ተናገሩ።
አማካሪው ማርክ ሚዶውስ እንዳሉት ኮቪድ-19ኝ መቆጣጠር የሚቻለው እንደ ክትባት እና መድሃኒት ሲገኝ ነው ብለዋል። አማካሪው ይህን ያሉት አሜሪካ ምርጫ ለማካሄድ 9 ቀናት በቀሩበትና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እየጨመረ ባለበት ወቅት ነው።
ዴሞክራቱ ተፎካካሪው ጆ ባይደን ደግሞ ዋይት ሃውስ የሽንፈት ባንዲራን እያውለበለበ ነው ብለዋል።
አክለውም ''የፕሬዝዳንቱ አማካሪ አስተያየት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ የመጀመሪያ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ማሳያ ነው'' ሲሉ ተደምጠዋል።
ማርክ ሚዶውስ ከሲኤኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር መሞከር አዋጪ እንዳልሆነና ምክንያቱ ደግሞ ቫይረሱ ልክ እንደ ማንኛውም ጉንፋን አይነት ባህሪ ስላለው ነው ብለዋል።
በአሜሪካ እስካሁን 225 ሺ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ይህ ቁጥር ደግሞ አገሪቱን ከዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ እንድትይዝ አድርጓታል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ብቻ አሜሪካ 83 ሺ 718 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን አርብ ዕለት ደግሞ 83 ሺ 757 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባ ነበር።
በአሜሪካ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝና ቫይረሱን ለመቆጣጠር መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ጉዳይ ከፍተኛ የምርጫ ክርከር ጉዳይ ሆኗል።
እስካሁን 59 ሚሊየን የሚሆኑ አሜሪካውያን ድምጻቸውን በፖስታ አማካይነት የሰጡ ሲሆን በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነም ተነግሯል።
በአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አንቶኒ ፋውቺ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለኮሮረናቫይረስ የሚሆን ክትባት ከዓመቱ መጨረሻ በፊት ዝግጁ ሊሆን እንደሚችልና የመጀመሪያዎቹ ብልቃጦች ግን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሰዎች እንደሚታደሉ ገልጸዋል።
አክለውም ክትባቱ ለመላው ሕዝብ ለማዳረስ በርካታ ወራትን ሊፈጅ እንደሚችልም ጠቁመዋል።