ሱዳን፡ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ልዑካን የአልበሽርን ላይ ውይይት ጀመሩ

አለም አቀፉ የወንጀሎች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ልዑክ አባላት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር የፍርድ ሂደት እንዴት ይካሄድ የሚለውን ለመወያየት ሱዳን መግባታቸው ተሰምቷል።

ኦማር አልበሽር ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር በተያያዘ ነው በፈርድ ቤቱ የሚፈለጉት።

ከዚህ በተጨማሪም በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያ እና ሌሎች ወንጀሎችም እንደሚፈለጉ የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የሱዳን መንግሥትም ቢሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተስማምቷል።

ነገር ግን በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል ከሚገኙ አማጺያን ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት መንግሽት ኦማር አልበሽርን ጨምሮ ሌሎች የጦር ወንጀለኞችን ጉዳይ የሚከታተል ልዩ ፍርድ ቤት ለማቋቋም ታቅዷል።

በአሁኑ ሰአት በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚገኘው የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ልዑክ ዋና አቃቤ ሕግ ፋቱዋ ቤንሶውዳን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት አለኝ በሚለው መረጃ መሰረት በአውሮፓውያኑ 2003 የጀመረው የዳርፉር አመጽን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል። ለዚህም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ተጠያቂ ናቸው ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት በተጨማሪ ሁለት የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ክስ መስርቷል። እነሱም አህመድ ሃሩን እና አብደልራሂም መሀመድ ሁሴይን ሲሆኑ በጦር ወንጀልና በሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የ76 ዓመቱ ኦማር አልበሽር ባሳለፍነው ዓመት ነበር ከፍተኛ ተቃውሞን ተከትሎ ከስልጣናቸው የተወገዱት። የሽግግር መንግሠዕት በአሁኑ ሰአት አገሪቱን እያስተዳደረ ሲሆን ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታትም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚቀጥል ይሆናል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከሚቀርብባቸው ክስ በተጨማሪ በሙስና ወንጀልም ተጠርጣሪ ናቸው።

እሳቸውና ሌሎች 27 የቀድሞ ባለስልጣናት ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1989 ወደ ስልጣን ያመጣቸውን መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘም በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ ነው የሚገኘው።

ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ከሆነ ደግሞ ሁሉም የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።

ኦማር አልበሽር ግን የቀረቡባቸውን ክሶች በሙሉ ክደው የተከራከሩ ሲሆን ጠበቆቻቸውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ገልጸዋል።