በእድሜ የገፉ አሜሪካውያን ለትራምፕ ምንም አይደሉም ሲሉ ባይደን ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ በፍሎሪዳ ያካሄዱትን የምርጫ ቅስቀሳ ዲሞክራቱ ፕሬዝደንታዊ እጩ ጆ ባይደን አጥብቀው ተቹ።

ለፕሬዝደንቱ "እናንተ መሰእዋት ናችሁ" ሲሉ ጆ ባይደን ለአዛውንት አሜሪካውያን ተናግረዋል።

ባይደን ይህን ያሉት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ በፍሎሪዳ ግዛት የመጀመሪያውን የምርጫ ቅስቀሳ ባደረጉበት ወቅት ነው።

እንደ ፍሎሪዳ እና ኦሃይዎ ያሉ ግዛቶች የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫን ለማሸነፍ ቁልፍ ግዛቶች ናቸው።

ከምርጫ በፊት ከሕዝብ የሚሰበሰቡ አስተያየቶች ባይደን ከትራምፕ የተሻለ ቀጣዩን ምርጫ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። በዚህም ምክንያት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከተቀናቃኛቸው ጋር ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ተያይዘውታል።

ከአራት ዓመት በፊት በነበራው ምርጫ ፍሎሪዳ ግዛት ላይ በእድሜ የገፉ አሜሪካውያን ለትራምፕ ድምጻቸውን መስጠታቸው ልዩነት ፈጥሮ ትራምፕ ተቀናቃኛቸው ሂላሪ ክሊንተንን በጠባብ ልዩነት ማሸነፍ ችለው ነበር።

ባይደን በደቡብ ፍሎሪዳ ግዛት ቁጥራቸው አነስተኛ ከሆኑ እድሜያቸው ከገፉ ደጋፊዎቻቸው ጋር ተገናኝተው ነበር።

ጆ ባይደን ፕሬዝደንቱ ኮሮናቫይረስ እድሜያቸው የገፋ አሜሪካውያን ላይ የሚያሳድረውን ጫና አቅልለው ተመልክተዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

ለትራምፕ "እናንተ መስዋእት ናችሁ፣ የምትረሱ ዜጎች ናችሁ፤ ለትራምፕ እናንተ ምንም ናችሁ። እድሜያቸው የገፉ ዜጎችን የሚመለከተው እንደዛ ነው" ሲሉ ባይደን ተናግረዋል።

ባይደን አዛውንቶች እራሳቸውን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ሲሉ የልጅ ልጆቻቸውን ማግኘት በማይችሉበት ወቅት ሪፓብሊካኖች ሊከሰት የሚችለውን መዘዝ ወደ ጎን በመተው በመተቃቀፍ ደስታ እና ድጋፋቸውን መለወዋጣቸው ስህተት ነው ብለዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ዲሞክራቱ ተቀናቃኛቸው "ጥሩ ሰው አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።