ጆርጅ ፍሎይድ፡ ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል የተጠረጠረው ፖሊስ በ1 ሚሊዮን ዶላር ዋስ ተለቀቀ

ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን ከመሬት አንገቱን በጉልበቱ አጣብቆ በመግደል የተከሰሰው የቀድሞ የአሜሪካ ፖሊስ በዋስ ከእስር ቤት መለቀቁ ተገለፀ።

የፍርድ ቤት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዴሪክ ቾቪን የተባለው ይህ ተጠርጣሪ ረቡዕ እለት በ1 ሚሊዮን ዶላር ዋስ ከእስር ተለቋል።

ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ጆርጅ ፍሎይድ ከመሞቱ በፊት፤ መሬት ላይ ተኝቶ ነጩ ፖሊስ ደግሞ አንገቱን በጉልበቱ ለ8 ደቂቃ ያህል አንቆ ይዞ፤ እስትንፋሱ እስክትቆም ድረስ ጆርጅ እንዲለቀው ሲማፀነው የሚያሳይ ቪዲዮ ተቀርጾ ነበር።

ቪዲዮው በርካቶችን ያስደነገጠ እና በመላው ዓለም 'የጥቁር ሕይወት ዋጋ አለው' [ብላክ ላይቭስ ማተር] የሚል ተቃውሞን አቀጣጥሎ ነበር።

የፍሎይድ መሞትን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞም የፖሊስ ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግም ጥሪ ቀርቧል።

ይህንን ተከትሎም ነጩ ፖሊስ ቾቪን ከሥራው የተባረረ ሲሆን ሆን ተብሎ በተፈፀመ የግድያ ክስ ፍርዱን እየተጠባበቀ ነው።

ጀ አሌክሳንደር ኩንግ ፣ ቶማስ ሌን እና ቶ ታኦም የተባሉ ሌሎች ሦስት ፖሊሶችም ከሥራቸው የተባረሩ ሲሆን ግድያውን ባለማስቆማቸውና በመተባበራቸው ተከሰዋል።

በሚኒሶታ፣ ሚኒያፖሊስ በተፈፀመው የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጋር ተያይዞ የተከሰሱት አራቱም ፖሊሶች በዋስ ወጥተው እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ነፃ ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ተወስኗል።

ቾቪን ከግንቦት ወር መጨረሻ አንስቶ በሚኒሶታ በሚገኘው ኦክ ፓርክ ሄይትስ እስር ቤት ነበር።

ይሁን እንጅ ባሳለፍነው ሰኔ ዳኛው በቅድመ ሁኔታ በ1.25 ሚሊየን ዶላር ወይም በቅድመ ሁኔታ በ1 ሚሊዮን ዶላር ዋስ እንዲወጣ ወስነዋል።

ቅድመ ሁኔታዎቹ የፍሎይድን ቤተሰብ እንዳያነጋግር፣ መሳሪያ እንዳይዝ፣ በሕግ አስፈፃሚ መሥሪያ ቤት ወይም በፀጥታ ሥራ እንዳይሰራ የሚሉትን ያካትታል።

ቾቪን በቅድመ ሁኔታ ባለው የገንዘብ ዋስ ከእስር እንደተለቀቀ እና የክስ መዝገቦቹ በዋስ ቦንድ ኤጀንሲ ዋስትና እንደተሰጣቸው የፍርድ ቤት መረጃዎች ማመልከታቸውን ሲቢኤስ ሚኔሶታ ዘግቧል።

በአሜሪካ ተከሳሾች የተጠየቁትን የዋስትና ገንዘብ መክፈል ካልቻሉ የዋስትና ቦንድ ወኪሎች ለተከሳሾች ሙሉ የዋስትና ገንዘብ ለመክፈል ቃል የሚገቡበት አሰራር አለ።

በዚህም መሰረት ቾቪን ረቡዕ ዕለት ከእስር መለቀቁን የሄኔፒን ግዛት ሸሪፍ ቢሮ መረጃ አመላክቷል።

የፍሎይድን ቤተሰቦች የወከሉት የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ቤን ክራምፕ፤ "ቾቪን በዋስ መለቀቁ 'ጥልቅ ህመም ቀስቃሽ' ነው፤ ለፍሎይድ ፍትሕ ለማግኘት አሁንም ሩቅ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።

" ምንም እንኳን ፍሎይድ በሕይወት እያለ ፍትሕ ቢነፈገውም፤ በሞቱ ሙሉ ፍትህ እስከሚያገኝ ድረስ አንተኛም" ብለዋል ክራምፕ።

አሁን ላይ ሁሉም ተከሳሽ ፖሊሶች መጋቢት ወር ላይ አንድ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዘዋል። ይሁን እንጅ ዳኛው ጉዳያቸውን በተናጠል ለማየት እንዳሰቡ ተነግሯል።

የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በአሜሪካ በዘር ልዩነት ላይ ያሉ ቁስሎች እንዲያመረቅዙ ምክንያት ሆኗል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቁጣ የተለወጠው የጥቁር ሕይወት ዋጋ አለው [ብላክ ላይቭስ ማተር] ተቃውሞ፤ በአሜሪካ ኅዳር ላይ ለሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የፖለቲካ ጉዳዮች አስኳል ሆኗል።

ጆርጅ ፍሎይድ ከመሞቱ 30 ደቂቃ በፊት የተፈጠረው ምን ነበር?

በአካባቢው ከነበሩ የአይን እማኞች፣ ቪዲዮና መግለጫዎች የሚታወቁት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው።

ካፕ ፉድስ ከተባለ አንድ መደብር ሲጋራ ገዛ። የመደብሩ ሠራተኛ ጆርጅ ፍሎይድ የሰጠኝ 20 ዶላር ሐሰተኛ ነው በማለት ፖሊስ ጋር ደወለ።

ቴክሳስ ተወልዶ ያደገው ጆርጅ ፍሎይድ በሚኒያፖሊስ መኖሪያውን ካደረገ ዓመታትን አስቆጥሯል።

በቅርቡም በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ በጠባቂነት ተቀጥሮ እየሰራ የነበረ ቢሆንም፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንደ በርካታ ሚሊዮን አሜሪካውያን ሥራ አልባ ሆኗል።

ጆርጅ ፍሎይድ የካፕ ፉድስ የተባለው መደብርም ደንበኛ ነበር።

በበርካታ ጊዜያትም እቃ እየመጣ እንደሚገዛ፣ ሁሉንም በትህትና ሰላም የሚል፣ በወዳጅነት የሚቀርብ ሰው እንደነበርም የመደብሩ ባለቤት ማይክ አቡማየለህ ለኤንቢሲ ተናግረዋል።

በዚያች መጥፎ ቀን ግን የመደብሩ ባለቤቱ ማይክ አቡማየለህ በሥራው ቦታ ላይ አልነበሩም።

በመደብሩ ተቀጥሮ የሚሰራው ታዳጊ የተጠራጠረውን ዶላር ሪፖርት አደረገ። ከ911 ጥሪ በተገኘው መረጃ መሰረት ታዳጊው ሲጋራውን መልስልኝ እንዳለውና ፍሎይድም አልመልስም እንዳለው ተናግሯል።

ሱቅ ሻጩ አስከትሎም ጆርጅ ፍሎይድ የጠጣ እንደሚመስልና ራሱንም መቆጣጠር አልቻለም ብሎ ተናግሯል።

ጥሪው ከተደረገ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ፖሊሶች ደረሱ። በወቅቱም ጆርጅ ፍሎይድ ከሁለት ግለሰቦች ጋር በአካባቢው የቆመ መኪና ውስጥ ተቀምጦ ነበር።

ወደ መኪናዋ ከተጠጉ በኋላ ቶማስ ሌን የተባለው ፖሊስ ሽጉጡን በማውጣት ከመኪናው እንዲወርድ ትዕዛዝ ሰጠው። በወቅቱ ሽጉጡን መምዘዝ ለምን እንዳስፈለገውም አቃቤ ሕግ ያለው ነገር የለም።

ቶማስ ሌን ለአቃቤ ሕግ በሰጠው የምስክርነት ቃል "እጅህን ወደላይ አልኩት እናም ከመኪናው ጎትቼ አወረድኩት" ካለ በኋላ "ጆርጅ ፍሎይድ በእጅ ሰንሰለት ለመታሰር አንገራግሯል" ብሏል።

ከታሰረ በኋላ ግን ጆርጅ ፍሎይድ ታዛዥ መሆኑን የገለፀው ፖሊሱ ቶማስ ሌንም "ሐሰተኛ ገንዘብ በመያዝ" እንደታሰረ ለጆርጅ መናገሩን አስረድቷል።

ከዚያም ወደመኪናቸው ሊያስገቡት ሲሉ ትግል እንደተፈጠረም ተገልጿል።

የስልክ ጥሪው ከተደረገ ከአስራ አራት ደቂቃ በኋላም ጆርጅ "ሰውነቱ ድርቅ ብሎ ተዝለፍልፎም መሬት ላይ ወደቀ። ለፖሊሶችም ጠባብ ቦታ እንደሚያፍነውና እንደሚያስጨንቀው መናገሩን" ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የስልክ ጥሪው ከተደረገ አስራ አራት ደቂቃ በኋላ ነበር ዴሪክ ቾቪን ቦታው ላይ የደረሰው።

እሱም ሆነ ሌሎች ፖሊሶች ከኋላ ሊጭኑትም እየሞከሩ ነበር። በዚህ ወቅት ነበር፣ በአስራ ዘጠነኛው ደቂቃ ቾቪን ጆርጅ ፍሎይድን መሬት ላይ የጣለው።

እጁን ታስሮ የነበረው ጆርጅ ፍሎይድም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ ነበር አንዲት ታዳጊ ሁኔታውን የቀረፀችው።

ጆርጅ ፊቱ ላይ መረበሽና መጨነቅም ይታይበት ነበር። የመጨረሻ እስትንፋሱም ሆነ ደቂቃዎች በቪዲዮ ተቀርፆም ለዓለም ሕዝብ ተጋርቷል።

በእጅ ሰንሰለት ታስሮ እንዲሁም በፖሊሶች ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ አንደኛው ነጭ ፖሊስም በጭንቅላቱና በአንገቱ መካከል የግራ ጉልበቱን ጭኖበት ነበር።

"መተንፈስ አልቻልኩም" በማለት በተደጋጋሚ ሲለምን እንዲሁም እናቱ እንድትደርስለት ሲማፀን የነበረው ጆርጅ "እባክህ፣ እባክህ፣ እባክህ" ሲልም ተሰምቷል።

ለዘጠኝ ደቂቃ ያህል የሚጠጋ (8 ደቂቃ ከአርባ ስድስት ሰድስት ሰኮንዶችም) በጉልበቱ አንገቱን እንደተጫነው ከአቃቤ ሕግ የተገኘ ሪፖርት ያሳያል።

ፖሊሱ አንገቱን ተጭኖት ስድስት ደቂቃ እንዳለፈው ነው ጆርጅ ፍሎይድ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማሳየት ያቆመው።