ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ውሻሽን እሰሪ ተብላ በጥቁር ሰው በመጠየቋ ለፖሊስ የደወለችው አሜሪካዊት ከስራዋ ታገደች
በኒውዮርክ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ ውሻሽን እሰሪ ብሎ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ የጠየቃት ግለሰብ ፖሊስ ጋር "እያስፈራራኝ ነው" ብላ መደወሏን ተከትሎ ከስራዋ ታግዳለች።
ግለሰቡ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙትን ወፎችንም ሆነ ሌሎች እንስሳቶች አደጋ ውስጥ ሊከት ይችላል በሚል ነው ውሻውን አስራ እንድትይዝ ነጯን ግለሰብ የጠየቃት።
ሴትዮዋም በበኩሏ " ለፖሊስ ደውዬ እናገራለሁ። አንድ ጥቁር (አፍሪካዊ አሜሪካዊ) ግለሰብ ለህይወቴ አስፈርቶኛል እላቸዋለሁ" በማለት ስትናገረውም ግለሰቡ በቪዲዮ ቀርጿታል።
የቫርቫርድ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ የሆነው ክርስቲያን ኩፐር የተባለው ግለሰብ ለፖሊስ እደውላለሁ እያለች ስታስፈራራ እንዲሁም ደውላ "ሊገድላት እንደሚችል" ስትደውልም የቀረፃት ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያውም አጋርቶታል። ቪዲዮውንም ከአስር ሚሊዮኖች በላይ ተመልክተውታል።
እሰጥ አገባው የተጀመረው ውሻው በሴንትራል ፓርክ የሚገኙ ዕፅዋትን ሲረጋግጥና ሲጫወት የተመለከተው ግለሰብ "ፓርኩ ላይ መልዕክቱ ተፅፏል። ውሻውን አስረሽ ያዥ እባክሽ" ብሎ የተናገራት ሲሆን፤ እሷም በምላሹ እንደማታስር ተናግራለች።
ፓርኩ በአካባቢው የተለያዩ ወፎችን መመልከት ለሚፈልጉ የታወቀ ስፍራ ሲሆን ዕፅዋቱንም እንዳያበላሻቸውም በመፍራት ለውሻው ምግብ ሰጥቶ ከቁጥቋጦው እንዲወጣ ለማድረግ ሞክሯል።
እሷም በሁኔታው በመበሳጨቷና እምቢ ማለቷን ተከትሎ ክርስቲያን ድንገት ወደ መጥፎ ሁኔታ ቢያመራ በማለት ለመረጃነት መቅረፅ የጀመረ ሲሆን እሷም በምላሹ መቅረፅ እንዲያቆምና "ለፖሊስ ደውዬ ጥቁር ሰው ሊገለኝ እያስፈራራኝ ነው ብዬ እነግራቸዋለሁ" ስትል የተሰማች ሲሆን ደውላም "አንድ ጥቁር ሰው ሊገለኝ እያስፈራራኝ ነው" ስትል ተሰምታለች።
ቪዲዮውም በትዊተር ላይ መጋራቱን ተከትሎ ግለሰቧ ከፍተኛ የሆነ ውግዘትና ውርጅብኝ እያስተናገደች ነው። በርካታ ጥቁሮች ያለ ምክንያት በፖሊስ በሚገደሉባት አሜሪካ እንዲህ አይነት ጥሪ ማድረጓ ዘረኝነት ነው ብለዋል።
በቅርቡም እየሮጠ በነበረበት ወቅት በሁለት ነጮች የተገደለውን የ25 አመቱን አህመድ አርበሪንም አስታውሰውታል።
"ስለ ጥቁር ሰዎች ባላቸው መጥፎ አስተሳሰብ ብቻ እንደ አህመድ አርበሪ ያሉ ግለሰቦች ተተኩሶባቸው በሚገደሉበት ዘመን ነው የምንኖረው። አንዱ መሆንም አልፈልግም" በማለት ክርስቲያን ተናግሯል።
የኒውዮርክ ፖሊስም በበኩሉ ቦታው ላይ ሲደርሱ ሁለቱም ግለሰቦች ባለመኖራቸው ክስም ሆነ እስር እንዳልተፈፀመ ኤንቢሲ ዘግቧል።
ኤሚ ኩፐር የተባለችው ግለሰብ በኋላ ይቅርታ ብትጠይቅም ከስራ ታግዳለች፤ ውሻውንም ስታንገላታውና ስታሰቃየው በመታየቷ ወዳመጣችበት መጠለያ እንድትመልስ ተደርጋለች።
አሰሪዋ ፍራንክሎን ቴምፕልተን ሁኔታው እስኪመረመር ድረስም ከስራ እንደምትታገድ በትዊተር ገፃቸው አስፍረው "የትኛውንም አይነት ዘረኝነትን አንቀበልም" ብለዋል።