ሩስያ፡ አሌክሲ ናቫልኒ፡ “ልሞት ይሆን? ብዬ አስብ ነበር”

አሌክሲ ከባለቤቱና ከልጁ ጋር
የምስሉ መግለጫ, አሌክሲ ከባለቤቱና ከልጁ ጋር

ተመርዞ የነበረው ሩስያዊው ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ ሰውነቱ እንዳሻው እንደማይታዘዘውና ቅዠትም እንደሚያስቸግረው ተናግሯል።

ሆኖም ግን እያገገመ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል። "በጣም እየተሻለኝ ነው" ያለው አሌክሲ ወደ ሩስያ እንደሚሄድም አስረድቷል።

ቢቢሲ አሌክሲን ያነጋገረው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቅ የበርሊን ሆቴል ውስጥ ነበር። እዛው በርሊን የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ለ32 ቀናት በጽኑ ህሙማን ማቆያ እንደነበረ አይዘነጋም።

ይቀዘቅዘውና ያንቀጠቅጠው የነበረ ቢሆንም ህመም እንዳልተሰማው ያስታውሳል።

"ምንም ህመም አልተሰማኝም። መጀመሪያ ላይ አንዳች ክፉ ነገር እንደገጠመኝ ተረድቻለሁ። ከዛ ግን ልሞት ይሆን? ብዬ ሳስብ ነበር።"

ነሐሴ 20 ከሳይቤሪያ ወደ ሩስያ እየበረረ ሳለ ነበር ህሊናውን የሳተው።

ሕይወቱ ሊተርፍ የቻለው አውሮፕላኑ አርፎ በአፋጣኝ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል በመወሰዱ ነው።

ከዛም ከሩስያ ባለሥልጣኖች ጋር ድርድር ተደርጎ ወደ በርሊን ተወስዷል። ሰመመን ውስጥ ገብቶም ነበር።

በኖቪቾክ መመረዙ ተረጋግጧል?

የኬሚካል መሣሪያን የሚቆጣጠረው የመንግሥታቱ ተቋም አሌክሲ በኖቪቾክ መመረዙን አረጋግጧል።

ይህ ጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደው መርዝ በአሌክሲ የሽንት እና ደም ናሙና ውስጥ መገኘቱንም ይፋ አድርጓል።

በፈረንሳይ እና በስዊዘርላንድ ቤተ ሙከራዎች የተሠራ ምርመራ አሌክሲ በኖቪቾክ መመረዙን እንደሚያረጋግጡ ጀርመን ተናግራለች።

ኖቪቾክ የተሠራው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በሶቪየት ሳይንቲስቶች ነበር። በጣም መርዛማ ስለሆነ ትንሹ መጠን ይገድላል።

አሌክሲ የተመረዘው በሩስያ እንደሆነ ተናግሯል። የሩስያ መንግሥት በቀጣዩ ዓመት የምክር ቤት ምርጫ ተፎካካሪ እንዳይሆን እንደመረዘውም አክሏል።

የሩስያ መንግሥት ግን እጄ የለበትም ብሏል። አሌክሲን የመረመሩት የሩስያ ሀኪሞች በሰውነቱ ምንም መርዝ አላገኘንም ብለዋል።

አሌክሲ ባለፈው ሳምንት ለጀርመን መጽሔት "ከድርጊቱ ጀርባ ያለው ቭላድሚር ፑቲን መሆኑን አምናለሁ። ሌላ አካል ሊሆን አይችልም" ብሎ ነበር።

አሌክሲ ከመታመሙ በፊት ሳይቤሪያ ውስጥ የጸረ ሙስና ቅስቀሳ እያደረገ ነበር።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ያሉት ሲሆን፤ ፑቲንን አጥብቆ በመተቸት ይታወቃል።

ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ከሩስያ ውጪ በስደት መኖር አልሻም ብሏል።

"ለረዥም ጊዜ ከሩስያ ሊያስወጡኝ ሞክረዋል። ከዚህ በኋላ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም። አላማ አለኝ፤ አገሬ አለችኝ" ሲልም ተናግሯል።

ቅዠት

አውሮፕላን ውስጥ ሳለ ሲመረዝ ምንም ነገር ላይ ለማተኮር እንዳልቻለ ያስታውሳል። በአካባቢው የነበሩ ሰዎችና ቁሳቁሶች ግን ደብዝዘው አይታዩትም ነበር።

ሆስፒታል ከገባ በኋላ በተደጋጋሚ ሲነቃ እንደነበርና ከሁሉም በላይ ይህ ስሜት እንደከበደው ይናገራል።

"ዘለግ ላለ ጊዜ ያቃዠኝ ነበር" ያለው አሌክሲ፤ በወቅቱ ባለቤቱ ዩሊያ፣ ሀኪሞች እና የመብት ተሟጋች ጓደኛው ሊዮንድ ቮልኮቭ አደጋ ደርሶበት እግሩን እንዳጣ የነገሩት እንደመሰለው ያስታውሳል።

ይህ ቅዠት እውነት እንደሆነ አምኖ ነበር። "አዲስ እግር በቀዶ ህክምና ይሰጠኛል" ብሎ ይቃዥም ነበር።

በተለይ ሌሊት ላይ ይህ ቅዠት ያሰቃየው ነበር።

"መተኛት አለመቻሌ ትልቁ ችግር ነው። ያለ እንቅልፍ ክኒን መተኛት አልችልም። ድሮ ግን እንዲህ ለመተኛት አልሰቃይም ነበር።"

በየጊዜው የሕክምና ክትትል ያደርጋል።

"አንዳንዴ ያለሁበትን ቦታ አልገነዘብም። በየቀኑ ሁለቴ በእግሬ እንሸራሸራለሁ። በጣም የሚከብደኝ ከመኪና መውጣት ነው" ይላል አሌክሲ።

ህመም ስለማይሰማው ደስተኛ ቢሆንም፤ ኳስ እንደመወርወር ያለ ቀላል እንቅስቃሴ ስለሚከብደው ያዝናል።