ላይቤሪያ፡ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ ገንዘብ የሚጠይቋቸውን ወጣቶች ተቹ

የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ ገንዘብ አልሰጡንም በሚል በርካታ ደጋፊዎቻቸው በስልክ የፅሁፍ መልዕክት የስድብ ናዳ እንደሚያወርዱባቸው ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ጉዳይ ይፋ ያወጡት በአንድ የቤተ ክርስቲያን ስነ ስርአት በተገኙበት ላይ መሆኑንም አፍሪካ ጋዜጣ ዘግቧል።

ጋዜጣው በፊት ገፁ ይዞት በወጣው ፅሁፍ ላይ ፕሬዚዳንቱ ከሚደርሳቸው 1 ሺህ የስልክ የፅሁፍ መልዕክቶች መካከል 999 ስድብ መሆናቸውንም ፕሬዚዳንቱን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በአንድ ወቅት አፍሪካ ካፈራቻቸው ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆነው የተመደቡት ጆርጅ ዊሃ በአሁኑ ወቅት ግማሹን የስልጣን ዘመናቸውን አጠናቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ሲመጡ ለወጣቱ የስራ እድል እፈጥራለሁ በማለት ቃል የገቡትንም መንግሥታቸው ማሟላት አልቻለም በሚልም ይተቻሉ።

በቤተ ክርስቲያኗ ለሚገኙ ምዕመናንም ክብራቸውን ለሚያዋርዱ ሰዎችም ምንም አይነት እርዳታ እንደማይለግሱም አስታውቀዋል።

"እርዳታዬን ጠይቃችሁ ፕሬዚዳንቱን ማዋረድ አይቻልም። እብሪተኛ ናችሁ፣ የጠየቃችሁኝ እኮ ትንሽ ነገር ነው። አልፈፅመውም" ማለታቸውንም ጋዜጣው አስፍሯል።

ፕሬዚዳንቱ በተለይም የትችት በትራቸውን ያሳረፉት በ19 እና 20ዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን ሲሆን ከቤተሰባቸው ጋር ከመኖር በራሳቸው መኖርን መርጠዋል ብለዋል።

"18 አመቴ እያለሁ መሬት ላይ ነበር የምተኛው። ለምን ለህይወት ትጣደፋላችሁ" በማለትም ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ያደጉት በመዲናዋ ሞኖሮቪያ ከአያታቸው ጋር ሲሆን በጎሮጎሳውያኑ 1995 ምርጡ የፊፋ ተጫዋች ሆነው መመረጣቸውንም ተከትሎ የአፍሪካ ምርጡ ተጫዋች ለመሆን በቅተዋል።

ወጣቶች በተለያዩ የቢዝነስ ስራዎች እንዲሰማሩ ጥረት እንዲያደርጉ የመከሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በራሳቸውም ለመኖር አትጣደፉ ብለዋል።

"አንዳንዶቻችሁ የቤት ኪራይ እንድከፍልላችሁ ጠይቃችሁኛል። እናትና አባት እያላችሁ ለምን እኔ ቤት ኪራይ እንድከፍል ትጠይቁኛላችሁ? ከእናታችሁ ጋር ለምን አትኖሩም። የቤት ኪራይ የምትከፍሉበትን ገንዘብ ከእናታችሁ ጋር አንድ ቢዝነስ ልታቋቁሙበት ትችላላችሁ" ብለዋል።