ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቲቤት ፡ ''ቻይና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በግዳጅ የጉልበት ሥራ እያሰራች ነው'' ሪፖርት
ቻይና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቲቤታውያንን ወታደራዊ መሰል የስልጠና ማዕከላው ውስጥ በማስገባት አስገዳጅ የጉልበት ሥራ እያሰራች እንደሆነ አንድ ጥናት ጠቆመ።
'ጄምስታውን ፋወንዴሽን' የተባለው ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ብሔራዊ መገናኛ ብዙሃን፣ የፖሊሲ ሰነዶች እንዲሁም ከሳተላይት የተገኙ ምስሎችን ዋቢ ያደረገ ሲሆን ሮይተርስ የዜና ወኪልም ምስሎቹን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ድርጅቱ በቲቤታውያኑ ላይ ተፈጸመ ያለውን ነገርም ከዚሀ ቀደም "በዊጋ ሙስሊሞች ላይ ከተፈጸመው ለይቼ አላውም" ብሏል። ነገር ግን የቻይና ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቲቤት በሂማሊያ ተራራዎች ዙሪያ የምትገኝ ግዛትና አብዛኞቹ ነዋሪዎቿ የቡድሀ እምነት ተከታዮች ናቸው። ቻይና ደግሞ ቲቤትን በአንድ ራስ ገዝ አስተዳደር መልክ የምትቆጣጠራት ሲሆን ብዙ ጊዜ ባህላዊና ሐይማኖታዊ ነጻነታቸውን በመጋፋት ትከሰሳለች።
የቤይጂንግ መንግሥት ግን ክልሉን ለማልማት በፈጣን እንቅስቃሴ ላይ ነኝ ይላል።
በአሁኑ ጊዜ በስደት ላይ የሚገኙት የቲቤት ፕሬዝዳንት ሎብሳንግ ሳንጋይ ከዚህ ቀደም ቻይና ቲቤታውያንን በማሰልጠኛ ካምፖች ውስጥ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ እያስገደደች እንደሆነና ማዕከላቱ በትምህርት ማስረጻ ስም እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸው ነበር።
ነገር ግን በድርጅቱ ጥናት መሰርት በአካባቢው እየተከናወነ ያለው ከዚህ በፊት ከታሰበው እጅግ በላቀ ሁኔታ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በጄምስታውን ፋወንዴሽን ስር ሪፖርቱን በዋነኛነት ያዘጋጁት ገለልተኛው ተመራማሪ አድሪያን ዤንዝ ሲሆኑ እሳቸው እንደሚሉት፤ 500 ሺህ የሚሆኑ ቲቤታውያን አብዛኛዎቻቸው ገበሬዎችና ከብት አርቢዎች ሲሆኑ በዚህ የፈረንጆች ዓመት 2020 ለሰባት ወራት በስልጠና ማዕከላቱ እንዲቆዩ ተደርገዋል።
የቻይና መንግሥት ግን ቲቤታውያኑን በስልጠና ማዕከላቱ የማቆያቸው ሥራ ባህሪያቸውን ለማሻሻል፣ የቻይና ቋንቋን ለማስተማርና በሥነምግባር ለማነጽ በማሰብ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስታውቋል።
መንግሥት አክሎም ሥራ መስራት አልችልም፣ ሥራ መስራት አልፈልግም እንዲሁም ምንም አያገባኝም የሚሉ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችን በስልጠና መቀየርና ለጊዜው ባልገተለጸ መልኩ ሰነፍ ሰዎችን "ማስወገድ" ዋነኛ አላማው እንደሆነ ገልጿል።
ጥናቱ ደግሞ የስልጠና ፕሮግራሞቹን ከጨረሱ በኋላ አብዛኞቹ ሰዎች እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ ያላቸው ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነና በተለይ ደግሞ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፣ በግንባታ እና የግብርና መስኮች የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ እተደረጉ መሆኑን አስነብቧል።
ጥናቱ በተጨማሪነትም ከዚህ በፊት የቻይና መንግሥት የዊጋ ሙስሊም ማኅበረሰቦችን በለይቶ ማቆያዎች በማስገባት ፈጽሞታል ከተባለው ተግባር ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ጠቁሟል።
"የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ" በሚል ሽፋን ለዓመታት የቆየው ይህ ካምፕ አስተሳሰብን የሚያጥብ፣ ጉልበትን የሚያዝል፣ እምነትን የሚሸረሽር፣ ኅቡዕ የግዞት ማዕከል ነበር ተብሏል።
ማቆያ ማዕከላቱ የዢንጂያንግ ነዋሪዎች የክህሎት ትምህርት የሚያገኙባቸውና አክራሪ የሐይማኖት አስተሳሰብን ለመቀነስ ትምህርት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ናቸው ይላሉ የቻይና ባለስልጣናት።
ነገር ግን አብዛኞቹ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በማዕከላቱ የሚገኙት ዜጎች ወደማዕከላቱ የሚወሰዱት እምነታቸውን በአደባባይ ስለገለጹ አልያም እንደ ቱርክ ባሉ የውጪ አገራት ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነው።