ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና እሥር ቤት ያሉ ሙስሊም ዜጓቿን እያሰቃየች ነው
ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይና ሾልከው የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ቻይናውያን በግዳጅ እምነታቸውን እንዲተው እየተደረጉ ነው።
በምዕራባዊዋ የቻይና ክፍል ዢንጂያንግ የሚገኙት 'ካምፖች' በፈቃዳቸው ለሚቀላቀሉ ዜጎች ትምህርት የሚሰጥበት ነው ስትል ቻይና ታስተባብላለች።
ነገር ግን ቢቢሲ ያገኛቸው ኦፊሴላዊ መረጃዎች እሥረኞቹ ተዘግቶባቸው እምነትና አስተሳሰባቸውን እንዲቀይሩ ስቃይ የበዛበት ቅጣት እንደሚደርስባቸው ያሳያሉ።
በእንግሊዝ የቻይና አምባሰደር መረጃዎቹን ሃሰተኛ ዜና ሲሉ ያጣጥሏቸዋል።
ቢቢሲ ፓናሮማን ጨምሮ ከሌሎች 17 ዓለም አቀፍ ሚድያዎች ጋር የሚሠራው ዓለም አቀፉ የመርማሪ ጋዜጠኞች ኮንሰሪተም ነው መረጃዎቹን ይፋ ያደረገው።
አንድ ሚሊዮን ገደማ ቻይናውያን እንደሚኖርባቸው የተጠረጠሩት እኒህ 'ካምፖች' ውስጥ በግዳጅ እንዲኖሩ የሚደረጉት አብዛኛዎቹ የዊገር ሙስሊሞች ናቸው ተብሏል።
ኮንሰሪተሙ ያገኘው አንድ ጥብቅ መረጃ የቀድሞው የዢንጂያንግ ክፍለ ግዛት ደህንነት ኃላፊ ለእሥር ቤቱ ኃላፊዎች የፃፉት ደብዳቤ ይገኝበታል።
ደብዳቤው ኃላፊዎቹ እሥር ቤቱን በጥብቅ ደህንነት እንዲያስጠብቁት፤ ከረር ያለ ዲስፕሊን እንዲከተሉ፤ ማንም ሊያመልጥ እንዳይሞክርና ከበድ ያለ ቅጣት እንዲጣል የሚያዝ ነው።
አልፎም ማንዳሪን የተሰኘው የቻይና ኦፊሴላዊ ቋንቋ ብቸኛው የመግባብያ ቋንቋ እንዲሆን፤ ኑዛዜ እንዲለመድ፤ ተማሪዎች ለውጥ እንዲያመጡ እና ካሜራዎች በሚታዩ ቦታዎች እንዲሰቀሉ የሚሉ ትዕዛዞችን ያዘለ ነው።
ሌላው ቀርቶ ተማሪዎች የሚተኙበት አልጋ አቀማመጥ፤ ለምግብ የሚሰለፉበት ሥነ-ሥርዓት፤ ትምህርት ቤት የሚቀመጡበት ሁኔታ አንዳች እንዳይዛነፍ ትዕዛዝ ተላልፏል።
ከቻይና መንግሥት ያመለጡት መረጃዎች ተማሪዎቹ አንዲት እንኳ ዲስፐልኢን ጥሰው ቢገኙ ከባድ ቅጣት እንዲመደርስባቸውና የእያንዷንዷ ደቂቃ ሕይወታቸው ክትትል እንደሚደረገበት ያሳያሉ።
ተማሪዎች ከእሥር ቤቱ የሚወጡት የምር ለውጥ አምጥተዋል ተብሎ ሲታመንባቸው እንደሆነም ተደርሶበታል።
አንደ ሌላ ያመለጠ ዶኪዩመንት ደግሞ የሌላ ሃገር ዜግነት ያላቸው የዊገር ሙስሊሞች ተለይተው እንዲታሠሩና ኑሯቸውን በሌሎች ሃገራት ያደረጉ ደግሞ በመኪና እንዲጋዙ መደረጋቸውን ያትታል።
በእንግሊዝ የቻይና አምባሰደር ሊዩ ዢያዎሚንግ እርምጃዎች ስኬታማ መሆናቸውን ለማስረገጥ ባለፉት ሶስት ዓመታት በቻይና አንዳችም የሽብር አደጋ አለመድረሱን ያነሳሉ።
የእያንዳንዱ ዜጋዋን የዕለተ'ለት ሕይወት ትሰልላች የምትባለው ቻይና በመብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ወቀሳ ይደርሳባታል።