ትራምፕ፡ ለዋይት ሀውስ መርዝ የላከችው ግለሰብ በአሜሪካና በካናዳ ድንበር ላይ በቁጥጥር ስር ዋለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሪሲን የተሰኘውን መርዝ የያዘ ጥቅል ልካለች በሚል የተጠረጠረች ሴት በቁጥጥር ስር መዋሏን የአሜሪካው የስደተኞች ቢሮ አስታውቋል።
ማንነቷ ያልተገለፀው ይህች ሴት በኒውዮርክ፣ ቡፋሎ ድንበር አቋርጣ ወደ ካናዳ ልትገባ ስትል መያዟ የተገለፀ ሲሆን የጦር መሳርያ ይዛ እንደነበርም ተዘግቧል።
ገዳይ የሆነውን መርዝ የያዘው ደብዳቤ ከካናዳ እንደተነሳ እንደሚታመን በስፍራው የሚገኙ መርማሪዎቹ ተናግረዋል።
ደብዳቤው የተገኘው ዋይት ሃውስ ከመድረሱ በፊት ባለፈው ሳምንት ነበር።
ሪሲን በተፈጥሮ የጉሎ (ካስተር) ፍሬ ውስጥ የሚገኝ መርዝ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋይት ሃውስ ላይ ጥቃት ለማድረስ የሚያስቡ ሰዎች ሲጠቀሙት ተስተውሏል።
የትራምፕ አስተዳደር እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
የፌደራሉ ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እና የደህንነት ቢሮው ጥቅሉን መመርመር የጀመሩት በአንድ በማቀነባበሪያ ድርጅት ውስጥ ወደ ዋይት ሃውስ ሊላክ እየተዘጋጀ ሳለ ነው።
ኤፍቢአይ "በዚህ ወቅት የታወቀ የሕብረተሰብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር የለም" ማለቱን ሲኤንኤን ዘግቧል።
ተጠርጣሪዋ በቴክሳስ ለሚገኙ አምስት የተለያዩ አድራሻዎች የሪሲን መርዝን የያዘ ጥቅል መላኳ የተጠረጠረ ሲሆን ከተላከላቸው መካከልም የማረሚያ እና የፖሊስ ቢሮዎች ይገኙበታል ተብሏል።
እንደ ባለስልጣናቶቹ መግለጫ ከሆነ በጥቅሎቹ ላይ ሪሲን የተሰኘው መርዝ መኖሩ የፋ የተደረገው ኤፍቢአይ በተደጋጋሚ ፍተሻ ካደረገ በኋላ ነው።
የካናዳ ፖሊስ ቅዳሜ እለት "ወደ ዋይት ሃውስ ከተላከ አጠራጣሪ ደብዳቤ ጋር በተያያዘ" ከኤፍ ቢአይ ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ተናግሮ ነበር።
ተጠርጣሪዋ ማክሰኞ እለት ቡፋሎ ውስጥ ፍርድ ቤት ትቀርባለች።
ሪሲን ገዳይ መርዝ ሲሆን ከተዋጠ፣ ወደ ውስጥ በትንፋሽ ከተሳበ፣ ወይንም በመርፌ ከተወጉት ማስመለስ፣ ማቅለሽለሽ ሊከሰት እንዲሁም የውስጥ አካል ሊደማ እና ስራ ሊያቆም ይችላል።
እስካሁን ድረስ ሪሲንን ለመፈወስ የሚያገለግል መድሃኒት መኖሩ አይታወቅም። ለመርዙ የተጋለጠ አንድ ሰው እንደ ወሰደው መጠን ከ36 ሰዓታት እስከ 72 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይሞታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጣር እንዳስታወቀው መርዙ፣ ለተለያዩ የሽብር ተግባራት እየዋለ የሚገኘው ይህ መርዝ፣ በዱቄት፣ በጤዛ እንዲሁም በእንክብል መልክ ሊዘጋጅ ይችላል።
ዋይት ሃውስ እንዲሁም ሌሎች የፌደራል መስሪያ ቤቶች ከዚህ ቀደምም ሪሲን የያዘ ጥቅል ተልኮላቸው ያውቃል።
በ2014 በሚሲሲፒ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ለባራክ ኦባማ እና ሌሎች ባለስልጣናት የሪሲን ብናኝ የተነከረ ደብዳቤ በመላኩ 25 ዓመት እስር ተፈርዶበት ወህኒ ተወርውሯል።
ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ የቀድሞ ወታደር ለፔንታጎንና ለዋይት ሀውስ መርዝ የያዘ ደብዳቤ በመላኩ ክስ ተመስርቶበታል።












