ኮሮናቫይረስ፡ በዓለማችን ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል

ከየትኛውም የዓለማችን አገራት በበለጠ በሕንድ ቫይረሱ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ከየትኛውም የዓለማችን አገራት በበለጠ በሕንድ ቫይረሱ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው

በጆንስ ሆፕኪንስ አሐዝ መሠረት በዓለም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሚሊዮን አልፏል። 940,000 ሰዎች ሞተዋል።

በወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አሜሪካ፣ ሕንድና ብራዚል ናቸው። አውሮፓ ውስጥ ደግሞ ቫይረሱ እያገረሸ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቫይረሱ በሁለተኛ ዙር የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ተጨማሪ የጥንቃቄ እርምጃዎች ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል ለሁለተኛ ጊዜ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ መጣሏ ይታወሳል።

አፍሪካ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። እየተካሄደ ያለው ምርመራ ቢጨምር ከዚህም በላይ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል መላ ምት አለ።

ክፉኛ የተጎዱ አገራት

በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳችው አሜሪካ ናት። 6.6 ሚሊዮን ሰው በበሽታው ሲያዝ 197,000 ሰዎች ሞተዋል።

አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከሐምሌ አንጻር እየቀነሰ ነው። በሕንድ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን አልፏል። ይህም በዓለም ሁለተኛው ከፍተኛ የህሙማን ቁጥር ነው።

በየቀኑ 90,000 ገደማ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ። የጽኑ ህሙማን አልጋና ኦክስጅን ውስን ሲሆን፤ 80,000 ሰዎች ሞተዋል።

በብራዚል 4.4 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። 34,000 ሰዎች ሞተዋል። ከአሜሪካ ቀጥሎ በርካታ ሰዎች የሞቱት በብራዚል ነው።

ፕሬዘዳንት ዣቪር ቦልሶናሮ ቫይረሱ የሚያስከትለውን ጉዳት በማቃለላቸው ተተችተዋል። ቫይረሱን ‘ትንሽዬ ጉንፋን’ ብለው የጠሩት ፕሬዘዳንቱ ሐምሌ ላይ በበሽታው ተይዘው እንደነበር አይዘነጋም።

ላቲን አሜሪካ ውስጥ አርጀንቲና እና ሜክሲኮም በበሽታው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በአርጀንቲና ከ600,000 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። በሜክሲኮ ደግሞ ቁጥሩ 680,000 ደርሷል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው አውሮፓ ውስጥ ቫይረሱ ማገርሸቱ እንደ ማንቂያ ደውል መታየት አለበት። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን የድርጅቱ የአውሮፓ ኃላፊ ሀንስ ክሉግ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ብቻ በአውሮፓ 300,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህም የወረርሽኙ ስርጭት ከጀመረበት ወቅት በላይ ነው።

እስካሁን አምስት ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙና ከ228,000 በላይ እንደሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ተስፋ አለ?

ውጤታማና አስተማማኝ ክትባት ለማድረግ በርካታ አገሮችና ተቋሞች እየተረባረቡ ይገኛሉ።

ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአሜሪካ ምርጫ በፊት ክትባት ይገኛል ብለው ነበር። የጤና ባለሙያዎች ግን የትራምፕ ንግግር ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።

ሩስያ ነሐሴ ላይ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቅዳለች። ይህም የመጀመሪያዋ አገር ያደርጋታል። የሩስያ ሳይንቲስቶች ክትባቱ በሽታ የመከላከል አቅም በማዳበር ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየቱን ተናግረዋል።

የሙከራ ሂደቱ የተገባደደ ክትባት የለም። ክትባት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ከሰዎች ጤና ይልቅ የፖለቲካ ጫና ያደረበት መሆኑ የሚያሰጋቸው ባለሙያዎች አሉ።

አሁን ወደ 150 ክትባቶች ላይ ምርምር እየተካሄደ ሲሆን፤ ክትባት የማግኘት ሩጫውን ሀብታም አገሮች ያሸንፋሉ ብለው የሚፈሩም አሉ።

ኮሮና
Banner