“ከኮሮናቫይረስ ባገግምም አሁንም በሽታው ይገድለኛል ብዬ እፈራለሁ”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ42 ዓመቱ ራጀሽ ቲዋሪ ከስልኩ የሰፋ መጠን ያለው ስክሪን ይፈራል። ቴሌቭዥን ወይም ኮምፒውተር አንዳች ጥቃት የሚያደርሱበት ፍጥረቶች ይመስሉታል።
ራጀሽ ቅዠት የጀመረው በጽኑ ህሙማን ክፍል ዘለግ ላለ ጊዜ ከቆየ በኋላ ነበር። ሰኔ ላይ ኮሮናቫይረስ ይዞት ስለተዳከመ በቬንትሌተር እየታገዘ እንዲተነፍስ ተደርጓል።
ራጀሽ ከሦስት ሳምንት በኋላ ተሽሎት ከሆስፒታል ቢወጣም ሙሉ በሙሉ እንዳላገገመ ተገነዘበ።
“ሕክምናው ቢያሽለኝም ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ የነበሩት የመጀመሪያ ሳምንታት በጣም ከባድ ነበሩ” ይላል።
ወደ ቤት ሲመለስ ቤተሰቦቹ እጅግ ተደስተው ነበር። ቆየት ሲል ግን ራጀሽ እንደ ቀድሞው እንዳልሆነ አስተዋሉ።
አንድ ቀን ቴሌቭዥን እያየ በጣም ጮኸ። ቲቪውን ለመስበርም ሞከረ። ከዛ በኋላ ቤተሰቡ ቲቪ መመልከትና ላፕቶፕ መጠቀም አቆመ።
ራጀሽ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ሳለ የተመለከታቸው የሕክምና መሣሪያዎችን ለመርሳት እየታገለ ነው።
የ49 ዓመቱ አሚት ሻርማም ተመሳሳይ ተሞክሮ አለው።
ለ18 ቀናት በለይቶ ማቆያ ሳለ በየቀኑ ሰዎች ሲሞቱ አይቷል። ወጣት፣ አዛውንት፣ ሴት፣ ወንድ. . . በርካታ የኮቪድ-19 ታማሚዎች በሞት ሲለዩ አሚት ተመልክቷል።
“ሁለት ሰዎች አጠገቤ ሞተው አስክሬናቸው ለረዥም ሰዓት አልተነሳም ነበር። ይህንን ከአዕምሮዬ ማውጣት አልቻልኩም። አሁንም ኮሮናቫይረስ ሊገለኝ ይችላል ብዬ እፈራለሁ” ይላል።
አሚት አሰቃቂ ቆይታውን ለመርሳት እየታገለ ነው። ከኮሮናቫይረስ ካገገመ በኋላ ጭምት ሆኗል። ካወራም በበሽታው ሳቢያ ስለሞቱ ሰዎች እንደሚያወራ አጎቱ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮቪድ-19 የሚያስከትለው የአዕምሮ ጤና ቀውስ
በሕንድ ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ቀውስ እየገጠማቸው ይገኛል።
የሥነ ልቦና ሀኪሙ ዶ/ር ቫሰንት ሙንድራ “ገና ሆስፒታል ሳይደርሱ አዕምሯቸው ይዳከማል። ከዛ ኮቪድ-19 ደግሞ የስሜት ህዋሳትን የበለጠ ያዝላል” ይላሉ።
ህሙማኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ አይፈቀድም። ሀኪሞቻቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ስለሚያደርጉም ፊታቸውን ማየት አይችሉም። ይህም ዶክተሮቻቸውን እንዳያምኑ ያደርጋቸዋል።
የኮሮናቫይረስ ህሙማን ሲያገግሙ ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። አስጨናቂ ክስተትን ተከትሎ የሚከሰት ድብት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም ዶ/ር ቫንሰት ያስረዳሉ።
ከኮሮናቫይረስ ህሙማን ጋር የተያያዘ የአዕምሮ ህመም ተገቢውን ትኩረት አላገኘም።
“በወረርሽኙ ወቅት እየታየ ያለው ሕንድ ለአዕምሮ ጤና ብዙም ቦታ እንደማትሰጥ ነው” የሚሉት ዶ/ር ሶሚትራ ፓትሬ ናቸው።
የአዕምሮ ህሙማንን ለማከም በቂ ሆስፒታል እንዲሁም ባለሙያዎች የሉም። በትንንሽ ከተሞች ደግሞ ችግሩ ይከፋል።
በከተማና በገጠር የሚኖሩ ሰዎች ለአዕምሮ ጤና ያላቸው ተደራሽነት እኩል አለመሆኑን ወረርሽኙ እንዳሳየ ዶክተሩ ይገልጻሉ።
“የሕንድ መንግሥት ችግሩን በአፋጣኝ ካልፈታ የአዕምሮ ህመም ወረርሽኝ ይገጥመናል” ሲሉም ያክላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለሙያው እንደሚሉት፤ የመጀመሪያው እርምጃ ሰዎች ስለ አዕምሮ ህመም ምልክቶች እንዲያውቁ ማድረግ ነው። በተለይም ለአነስተኛ ከተማ ነዋሪዎች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
በደልሂው ፎርቲስ ሆስፒታል የአዕምሮ ጤና ክፍል ኃላፊ ካምና ቺቤር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በርካታ ሰዎች የአዕምሮ ህመም እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
የእንቅስቃሴ ገደቡና ወደፊት ምን እንደሚከሰት አለማወቅ ብዙዎችን ጭንቀትና ድብርት ውስጥ ከቷል።
“ችግሩ ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ ነው” ብለዋል ኃላፊዋ።
በድህረ ኮቪድ-19 ማገገሚያ እቅድ የአዕምሮ ጤና ጉዳይ እንዲገባ በርካታ ሀኪሞች እየጠየቁ ነው።














