አሜሪካ፡ ዶናልድ ትራምፕ "ሳይንስ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም" ሲሉ አጣጣሉ

በኅዳር ወር ለዳግም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ማወዛገባቸውን ቀጥለዋል፡፡

ትናንት የሰደድ እሳት የበላውን ምዕራቡን የአሜሪካ ክፍል ለመጎብኘት ካሊፎርኒያ ነበሩ፡፡

የካሊፎርኒያ ሰደድ እሳት ሰፊውን የካሊፎርኒያ ግዛትን ብቻ ሳይሆን ኦሪጋንና ዋሺንግተን ግዛቶችን ጭምር ያካለለ በታሪክ ሰፊ ቦታን ከሸፈኑ ሰደድ እሳቶች አንዱ ነው፡፡

እሳቱ የበላው ጫካ ምን ያህል ይሰፋል ቢባል ከሎንዶን ወይም ከኒውዮርክ ከተሞች በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

ሁለቱ ከተሞች ቢደመሩም ሰደድ እሳቱ ካካለለው ቦታ ያንሳሉ፡፡

ወይም ደግሞ 10 ኒውዮርክ ከተማዎችን ያክላል በመጠን፡፡

ወይም በሌላ አነጋገር በየ 24 ሰዓቱ ዋሺንግተን ዲሲን የሚያህል መሬት በእሳት ይበላል፡፡

በሌላ አሐዛዊ አነጋገር ሰደድ እሳቱ ያወደመው ቦታ ስፋት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሆኗል፡፡

በእሳት አደጋው እስከ አሁን 35 ሰዎች ሞተዋል፡፡

የዚህ ሰደድ እሳት ዋንኛ ምክንያት አየር ንብረት ለውጥ እንደሆነ ሳይንስ ቢናገርም ትራምፕ በሳይንስ ተሳልቀዋል፡፡

ከካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪዎች ጋር የተገናኙት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አይዟችሁ እሳቱ በራሱ ጊዜ ይጠፋል› ብለዋቸዋል፡፡

እሳቱ ከነሐሴ ወር መጀመርያ የጀመረ ዛሬም ድረስ አልጠፋም፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ብሎ ነገር የለም የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ ለሰደድ እሳቱ ዋናው ምክንያት የጫካ አስተዳደር ድክመት ስለሆነ እሱን ማጠናከር ነው ብለዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ዌስት ኮስትን ከጎበኙ በኋላ ከአካባቢው ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ውይይት አንድ ኃላፊ ሳይንስና የአየር ንብረት ለውጥ እስከነ አካቴው ገሸሽ መደረግ እንደሌለባቸው ሲያነሱ ዶናልድ ትራምፕ ሰውየውን አቋርጠው ‹‹ሳይንስ ምን ያውቃል? ሳይንስ ምንም የሚያውቅልህ ነገር የለም›› ብለዋቸዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንድትወጣ ያደረጉ መሪ ናቸው፡፡

ከዚህ ስብሰባ በኋላ አንድ ጋዜጠኛ ዶናልድ ትራምፕን ‹‹ለመሆኑ የሰደድ እሳት መልሶ መላልሶ የሚያጠቃን ጉዳይ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ ይሆን ወይ ሲል ጠይቋቸው ነበር፡፡

‹‹አይደለም፤ ዋናው የጫካዎችን አስተዳደር ማስተካከል ነው›› ብለውታል፡፡