ኮሮናቫይረስ፡ ቱርካዊቷ መምህርት ኢንተርኔት ለሌላቸው ተማሪዎች በየቤታቸው እየሄደች ማስተማር ጀመረች

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አገራት በርካታ መመሪያዎችን አውጥተዋል።

ከነዚህም መካከል እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ መገደብና ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ይገኙበታል። በበርካታ ከተሞች በተለይ አቅማቸው የተጠናከሩ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ትምህርት እንዳያመልጣቸው በማለት በበይነ መረብ የሚሰጠውን ትምህርት እንዲከታተሉ አድርገዋል።

አቅሙ ወይም አቅርቦቱ የሌላቸውስ? በምስራቃዊ ቱርክ በምትገኘው ቫን ግዛት የምትገኝ ጋምዜ አርስላን የተባለች መምህርት በበይነ መረብ ትምህርታቸውን መከታተል ለማይችሉ ተማሪዎች ቤት ለቤት እየዞረች ትምህርት ትሰጣለች።

"በትምህርት ቤታችን ውስጥ ኢንተርኔት አለ ነገር ግን በዚያ ማስተማር እልቻልንም። ምክንያቱም በርካታ ወላጆች በቤት ውስጥ ኢንተርኔት የላቸውም" በማለት ሃበርቱርክ ለተባለው የዜና ወኪል ተናግራለች።

"ነጭ ሰሌዳዬን ይዤ ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እየሄድኩ አስተምራለሁ" በማለት የምትናገረው ጋምዜ በቫን ቱስባ ግዛት ውስጥ ያሉ መንደሮችንም ማካለል አለባት።

በየቀኑም ማስተማር፣ የቤት ስራቸውን በአግባቡ ሰርተው እንደሆነ መቆጣጠርና መከታተል ከዚያም በተጨማሪ አካላዊ ርቀታቸውንና ንፅህናቸውን በጠበቀ መልኩ የመማር የማስተማር ሂደቱ እንዲከናወንም ዋናው ኃላፊነት የሷ ነው።

የጋምዜ መልካም ተግባር ከተሰማ በኋላ በርካቶች እያሞገሷትና እያወደሷት ይገኛሉ። የተለያዩ ሚዲያ ቀልብንም መሳብ ችላለች።

"ኢንተርኔት ላይኖር ይችላል ግን መምህርት ጋምዜ አለች" በሚልም በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ፕሮግራም ተሰርቶላት ነበር።

የአካባቢው ባለስልጣናት ቢሆን ምስጋና ችረዋታል።

"ግዛታችን እንዲህ ባለ ፈታኝ ወቅትና አቅመ ቢስነት በተሰማን ወቅት እንዲህ አይነት አማራጭ በመኖሩ ደስተኛ ነን " በማለት የቱስባ የትምህርት ዳይሬክተር መህመት ባኪር ቤድቪዮግሩ ለሃበርተርክ ተናግረዋል።

"ይህ ተግባሯ እንደ መስዋዕትነት በተምሳሌትነት የምናየው ነው። እንዲህ አይነት ሳይሰስቱ መስጠትን ልምድ እንድናዳብር ምሳሌ ይሆነናል" ብለዋል።

በርካታ የአውሮፓ አገራት ትምህርት ቤቶችን ቢከፍቱም ቱርክ ግን በተወሰነ መልኩ ለመክፈት ከአንድ ወር በኋላ አቅዳለች።

ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሚዲያዎች ለወራት ያህል ተማሪዎች የኢንተርኔት አቅርቦት ስለሌላቸው ችግር እያጋጠማቸው ነው በማለትም ሲተቹ ነበር።