የሴቶች ጥቃት፡ የ86 አመት የእድሜ ባለፀጋ አያት መደፈር መላ ህንድን አስደንግጧል

የመደፈር ጥቃት ከፍተኛ በሆነባት ህንድ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በየአመቱ ይደፈራሉ።

አንዳንድ ጥቃቶች ደግሞ ጎልተው ይወጡና በርካቶችን ያስደነግጣሉ።

ከሰሞኑም በህንዷ መዲና ደልሂ የ86 አመት እድሜ ባለፀጋ አያት መደፈራቸውን ህንድን አንቀጥቅጧታል። የእድሜ ባለፀጋዋን በመድፈር በ30ዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ግለሰብ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏል።

ግለሰቧ በዚህ ሳምንት ሰኞ እለት ወተት የሚያመጣላቸውን ሰው እየጠበቁ ባለበት ወቅት ጥቃት እንደደረሰባቸው የደልሂ የሴቶች ኮሚሽን ስዋቲ ማሊዋል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ጥቃት አድራሹ ወተት የሚያመጣላቸው ግለሰብ እንደማይመጣና ወተት የሚመጣበት ስፍራ ልውሰድዎት አላቸው" ብለዋል።

አያቲቷ ምንም ባለመጠራጠር ግለሰቡን ተከትለውት የሄዱ ሲሆን ቀረብ ወዳለ እርሻ ቦታም በመውሰድ እንደደፈራቸው ስዋቲ አስረድተዋል።

"እያለቀሱም እንዲተዋቸው ለመኑት። አያቱ ማለት እንደሆነም ተማፀኑት። ግን ልመናቸውም ሆነ መማፀናቸው ትርጉም አልነበረውም። ራሳቸውን ለመካለከልም ሲታገሉ ክፉኛ ድብደባ ፈፅሞባዋቸዋል። ከዚያም ደፈራቸው" ብለዋል።

በአካባቢው ሲዘዋወሩ የነበሩ ነዋሪዎች ለቅሷቸውን ሰምተው እንዳዳኗቸው ተነግሯል። ግለሰቡንም በቁጥጥር ስር በማዋል ለፖሊስ አሳልፈው ሰጥተዋል።

ስዋቲ ማሊዋል ጥቃት የደረሰባቸውን የእድሜ ባለፀጋ ማክሰኞ እለት በቤታቸው ሄደው የጎበኟቸው ሲሆን፤ ካዋሯቸውም በኋላ ሁኔታቸውን"ልብ የሚሰብር" ብለውታል።

"እጃቸው ተላልጧል። ያለፉበትን ለሰማ በጣም የሚያስደነግጥ ነው። ፊታቸው አባብጧል፤ ሰውነታቸው ቆስሏል። ብልታቸውም እየደማ ነበር። ከፍተኛ የሆነ ድብደባም ተፈፅሞባቸዋል። የደረሰባቸውን ሰነ ልቦናዊ ጉዳት በቃላት መግለፅ ይከብዳል" በማለትም ኃዘናቸውን ገልፀዋል።

ስዋቲ ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን " ሰው አይደለም" በማለት ጠንከር ባለ ቃል ተናግረዋል።

"በደልሂ ለሚገኙ የፍትህ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ግለሰቡን በስድስት ወራት ውስጥ በስቅላት እንዲቀጡትም ደብዳቤ ፅፌያለሁ" በማለት የሚገባውን ቅጣትም ገልፀዋል።