የትግራይ ምርጫ፡ ትልልቆቹ የህወሓት እጩዎች የት ተወዳደሩ?

በኢትዮጵያ በነሐሴ መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ከተላለፈ በኋላ በትግራይ በተናጠል የሚካሄደው ምርጫ ሕገ ወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢወስንም ዛሬ እየተካሄደ ነው።
ለወራት በፌደራሉና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ያለመግባባት ምንጭ ሆኖ የቆየው ክልላዊው ምርጫ ዛሬ ጳጉሜ 04/2012 ዓ.ም አገሪቱ ካሏት 10 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በተለየ በትግራይ ክልል ውስጥ ይካሄዳል።
በዚህ ምርጫ ላለፉት 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በብቸኝነት በህወሓት ተይዞ ለቆየው የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች 5 ፓርቲዎቹ ይወዳደራሉ።
በምርጫው ተቃዋሚዎች ሰምሮላቸው የትኛውንም ያህል መቀመጫ ቢያገኙ በክልሉ ታሪክ በምክር ቤቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከህወሓት ውጪ የሆነ ድምጽ የመሰማት ዕድል ያገኛል።
በዚህ ምርጫም ከህወሓት አንጻር በክልሉ የፖለቲካ መድረክ ላይ አዲስ የሆኑት አራት ፓርቲዎች ለፉክክር ቀርበዋል። እነርሱም ሳልሳይ ወያኔ፣ ባይቶና፣ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ እና የአሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሲሆኑ አራት ግለሰቦች በግል ይወዳደራሉ።
በምርጫው የሚሳተፉት ፓርቲዎች ባካሄዷቸው ክርክሮች ላይ እንዳንጸባረቁት በተለያዩ መስኮች ካሏቸው ፕሮግራሞች ባሻገር ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት አንስተው ዓላማቸውን አንጸባርቀዋል።
በዚህም ክልሉ በፌደራላዊ ሥርዓት ከቀሪው የአገሪቱ ክልሎች ጋር ተሳስሮ እንዲቀጥል ከመፈለግ አንስቶ በኮንፌዴሬሽን የላላ ግንኙነት እንዲኖር የሚፈልጉና ከዚህም ከፍ ሲል ነጻ ሪፐብሊክ የመመስረት ፍላጎትም ተንጸባርቋል።
በዚህ ምርጫ 190 መቀመጫዎች ላሉት ምክር ቤት 625 እጩዎች ለመወዳደር ቀርበዋል። ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምጽ ለመስጠት እንደተመዘገበ ያስታወቀው የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ድምጽ መስጠቱ የሚከናወንባቸው 2684 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ አስታውቋል።
ክልሉ ምርጫውን እንዲያስፈጽምለት ብሔራዊውን የምርጫ ቦርድን ቢጠይቅም ካለው የወረርሽኝ ሁኔታ አንጻር በመላው አገሪቱ ከተወሰነው ውጪ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል አሳውቆ ጥያቄውን ሳይቀበለው መቅረቱ ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ነበር ክልሉ ከራሱ በጀት በማውጣት የምርጫ ኮሚሽን መስርቶ ምርጫውን ለማካሄድ በመወሰን ከዛሬው የድምጽ መስጫ ቀን ላይ የተደረሰው።
ዋነኞቹ የህወሓት እጩዎች
በፌደራል መንግሥቱና በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው ዋና ዋና የህወሓት አባላት በዚህ በምርጫው በተለያዩ ጣቢያዎች ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ለውድድር ቀርበዋል።
የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንትና የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ በአድዋ ከተማ ፓርቲያቸውን ወክለው ሲወዳደሩ፣ እዚያው አድዋ ውስጥ ባሉ ቦታዎች ላይ ደግሞ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የቀድሞዋ የንግድ ሚኒስትር ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ) እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ይወዳደራሉ።
በመቀለ የምርጫ አካባባቢ ህወሓትን ወክለው ከሚወዳደሩት መካከል በገዛ ፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ከጥቂት ወራት በፊት የለቀቁት የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም፣ በሕግ የሚፈለጉት የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር የአቶ ጌታቸው አሰፋ ወንድም ዳንኤል አሰፋ በዕጩነት ቀርበዋል።
የአዲግራት ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክትር ዛይድ ነጋሽ በአዲግራት የህወሓት እጩ ሆነው ቀርበዋል።
የቀድሞው የኮሙኑኬሽን ሚኒስትርና በተለያዩ የማዕከላዊው መንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ህወሓትን ወክለው አላማጣ ውስጥ ሲቀርቡ የመቀለ ዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ክንደያ ገብረሕይወት (ፕሮፌሰር) እንደርታ በመቀለ አካባቢ ቀርበዋል።
በተለያዩ የምርጫ አካባቢዎች ህወሓት ከተጠቀሱት በተጨማሪ በርካታ እጩዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ተፎካካሪዎችም ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮቻቸውን ጨምሮ በርካታ አባሎቻቸውን በምክር ቤቱ ውስጥ መቀመጫ ለመያዝ በዕጩነት አቅርበዋል።
ቀደም ሲልም የክልሉ ምክር ቤት ከዚህ በፊት ሲሰራበት የነበረውን የአብላጫ ድምጽ የውክልና ሥርዓት በመቀየር ቅይጥ ትይዩ በሚባለው የውክልና ሥርዓት እንዲተካ ወስኖ፣ ይህም አሁን በሚካሄደው ምርጫ ተግባራዊ ይሆናል። ይህም ፓርቲዎች በአጠቃላይ ከሚያገኙት ድምጽ አንጻር በምክር ቤቱ ውክልና እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።
በተጨማሪም በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ መቀመጫዎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ አብላጫ ድምጽ ባገኘው የፖለቲካ ድርጅት የሚያዙ ሲሆን፤ 20 በመቶው ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና ለተወዳዳሪ ድርጅቶች እንዲከፋፈል ይደረጋል ተብሏል።
















