የአውሮፓ ሕብረት ፡ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ከ8 ሰዎች አንዱ ይሞታል

በአውሮፓ ሕብረት አገራት ውስጥ ከሚሞቱ 8 ሰዎች መካከል የአንድ ሰው ሞት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንደሚያያዝ የአውሮፓ ሕብረት የአካባቢ ጥበቃ አጀንሲ ሪፖርት ጠቆመ።

በሕብረቱ አገራት ውስጥ ለሚሞቱ ሰዎች የአየር ብክለት፣ የውሃ ንጽህና ጉድለት እና የኬሚካል ተጋላጭነት ምክንያት እንደሆነና ይህም የ13 በመቶ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት እንደሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሪፖርቱ ጨምሮ እንዳለው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ የማኅብረሰብ ክፍሎች ለአየር ንብረት ለውጥ የበለጠ ተጋላጮች ናቸው።

በዚህም ምክንያት "በአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ ማኅብረሰቦችን ለመጠበቅ ጠንከር ያለ እርምጃ ያስፈልጋል" ብሏል ኤጀንሲው።

የሕብረቱ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ኮሚሽነር ቪርጂኒጅስ ሲነኬቪሲየስ እንዳሉት የሰው ልጆች ጤና እና ከባቢያዊ አየር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው።

"እያንዳንዱ ሰው ሊረዳው የሚገባው ነገር የአካባቢያችንን ሥነ-ምህዳር መንከባከብ ቻልን ማለት የሰዎችን ህይወትን እየታደግን ነው ማለት ነው" ብለዋል።

መቀመጫውን ኮፐንሃገን ያደረገው ኤጀንሲው ትናንት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ እአአ በ2012 በአውሮፓ ሕብረት አገራት ውስጥ ለ630 ሺህ ሰዎች ሞት የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ምክንያት ነው ብሏል።

የአየር ብክለት ለ400 ሺህ ሰዎች ሞት እንደ አንዱ ምክንያት ሆኖ የቀረበ ሲሆን፤ የድምጽ ብክለት ደግሞ ከ12 ሺህ ሰዎች ሞት ጋር ተያይዟል። የተቀሩት ደግሞ እንደ ከፍተኛ ሙቀት ካሉ የአየር ሁኔታዎች ጋር ተያይዘዋል።

ሪፖርቱ የሰው ልጆች በየትኛው ጊዜ ለአየር፣ ለውሃ፣ ለድምጽ ብክለት ወይም ለኬሚካል ተጋላጭ ናቸው ይላል። እነዚህም በተናጠልም ሆነ በድምሩ በሰው ልጆች ጤና ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ነው ብሏል።

ኤጀንሲው በሪፖርቱ እንደገለጸው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከአውሮፓ አገራት ብዙ ጉዳት እያስተናገዱ የሚገኙት የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ናቸው።

እንደምሳሌ የኖርዌይ እና የአይስላንድ ዜጎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባቸው ጉዳት ከአልባኒያ አንዲሁም ከቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

የዓለም ጤና ድርጅትም ከዚህ ቀደም የአየር ብክለት በመላው ዓለም ለሚሊዮኖች ሞት ምክንያት እየሆነ ነው ብሎ ነበር። የአየር ብክለት ከስትሮክ፣ ከሳምባ ካንሰር እና ከልብ ሕመም ቀጥሎ የበርካቶችን ሕይወት ይቀጥፋል ይላል ድርጅቱ።

ሌላ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደጠቆመው ደግሞ የድምጽ ብክለት የደም ግፊት መጠንን ከፍ በባመድረግ እና የጨንቀት ሆርሞኖች እንዲመነጩ በማደረግ ለልብ ሕመም ያጋልጣል ብሏል።