ቤንሻንጉል ጉሙዝ፡ በክልሉ በደረሰው ጥቃት የፀጥታ ኃይሎች መጎዳታቸው ተገለፀ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች በተፈጠረ አለመረጋጋት የፀጥታ ኃይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የህክምና ባለሙያ ለቢቢሲ እንዳስታወቁት በሚሠሩበት ቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ትናንት ምሽት ከአንድ ሰዓት በኋላ ጉዳት የደረሰባቸው የመከላከያ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የልዩ ሃይል አባላት የህክምና ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ትናንት ህክምና የተደረገላቸው ከትናንት ወዲያ ጉዳት የደረሰባቸው የጸጥታ ኃይል አባላት መሆናቸውንም ጨምረው አስታውቀዋል።

የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያው አክለውም በሆስፒታላቸው ሁለት የመከላከያ አባላት ህይወታቸው አልፎ አስከሬናቸውን መመልከታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

እንደባለሙያው ከሆነ የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ የመጡት የጸጥታ ኃይል አባላት ስምንት ሲሆኑ አምስቱ የመከላከያ ሠራዊት፣ ሦስቱ ደግሞ የልዩ ኃይል አባላት ናቸው።

የጸጥታ አካላቱ ህክምና ከተደረገላቸው በኋላ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ ወደ ባህር ዳር የመከላከያ ሠራዊት ሆስፒታል የክልሉ የልዩ ኃይል አባላት ደግሞ ወደ ፓዊ ሆስፒታል መላካቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

ባለሙያው ወደ አካባቢዎቹ ተጨማሪ የጸጥታ አካላት ሲገቡ መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

ስለጉዳዩ ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ በጉዳዩ ላይ ስምሪት የተሰጠው የጸጥታ አካል መረጃ በሚሰጣቸው ጊዜ ትክክለኛ መረጃ ከመስጠት ውጭ አሁን መረጃ በደፈናው መስጠት የተሟላ አይሆንም ብለዋል።

"በየአቅጣጫው የሚወራውን አሉባልታ መንገርም ለመረጃ የሚጠቅም ስለማይሆን፤ አንዳንድ አላስፈላጊ አሉባልታዎች ሊሆኑ ስለሚችሉ እሱን እንደ መረጃ መውሰድ አያስፈልግም። በእኛ በኩል ወደ አካባቢው የገባ የጸጥታ አካል አለ። ሥራውን ሠርቶ ሲወጣ ወይም ደግሞ በመሃል ላይ መረጃ ለመስጠት አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ የተሟላ መረጃ በዚያ መልክ እንሰጣለን" ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በአካባቢው ያለው ሁኔታ ከጸጥታ አካላቱ አቅም በላይ አለመሆኑን ጠቁመው፣ የጸጥታ ኃይሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመግባት ህዝቡን በማረጋጋት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም 'ጸረ ሠላም' ያሏቸው ኃይሎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው የተሟላ መረጃ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

"የጸጥታ አካሉ እዚያ ያለው ኔትዎርክ ደካማ በመሆኑ መረጃ ለማግኘት ትንሽ ተቸግረናል" ያሉ ሲሆን "የገባው የጸጥታ አካል ወጣ ብሎ ኔትዎርክ ያለበት ቦታ ሲሆን ነው ደውሎ መረጃ መስጠት የሚችለው። እና መረጃ ለመስጠት በኔትዎርክ ችግር ምክንያት አልቻልንም። እነሱ እንደወጡ መረጃውን ማድረስ እንችላለን" ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

'የጸረ ሠላም ኃይሎች' ያሏቸው አካላት ከህብረተሰቡ ጋር የተቀላቀሉ መሆኑ እርምጃ ለመውሰድ ትንሽ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመው ከሠላማዊ ህብረተሰብ የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአካባቢው የተፈጠረው ችግር ከአንድ ወር በፊት በጉባ ከነበረው ጥቃት ጋር የተያያዘ መሆኑን ኮማንደር ነጋ ጠቁመው፣ በወቅቱ የጸጥታ አካለት በሠሩት ሥራ ተጠርጣሪዎችን ከነጦር መሣሪያቸው በመያዝ ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ጉባ ወረዳ ሠላማዊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በመተከል ዞን በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች የጸጥታ አካላት ከገቡ በኋላ አንጻራዊ ሠላም መፈጠሩን አክለው አስረድተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ባሉ ሁለት ወረዳዎች በቡድን የተደራጁ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የክልሉ ፖሊስ ለቢቢሲ በትናንትናው እለት ገልጿል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ለቢቢሲ እንደገለጹት "ፀረ ሠላም" ያሏቸው ኃይሎች በወንበራ ወረዳ መልካ በምትባል ቀበሌ ሠላማዊ ሰዎችን በማገት፣ የጦር መሣሪያዎችን በመቀማትና በአካባቢው ማኅበረሰብ ንብረት ላይ ዘረፋ ፈጽመዋል ብለዋል።

በቤንሻንጉል ክልል የተፈጠረው ምንድን ነው?

በትላንትናው ዕለትም [ሰኞ] በቡለን ወረዳ ኤጳር በምትባል ቀበሌ እነዚሁ ኃይሎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የአፈናና የግድያ ወንጀል ከመፈጸማቸው በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በአካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ጠይቆ እንደተረዳው በተለያዩ ጊዜያት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሚፈጸመው ጥቃት የተነሳ የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በስጋት ውስጥ ሆነው እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

በሚፈጸሙት ጥቃቶችም በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው መገደቡንና ክስተቱም ሁሉም በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረጉ በአካባቢዎቹ ባለው ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ የጤናና ግብርና ባለሙያዎችን ለማፈን ከመሞከራቸውም በላይ በመንግሥት መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ወደ ሌላ ወረዳ መሸሻቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ በወጣው መረጃ መሰረት የአካባቢው ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ ልዩ ኃይል በጋራ በመሆን ወደ ወረዳዎቹ በመግባት ጥቃቱን ለማስቆምና ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ በወረዳዎቹ እንደሚሉት ጉዳት እያስከተለ ያለው ጥቃት የሚፈጸመው ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ባልፈለጉት "የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን አባላት" መሆኑንና በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስካሁን የታገቱ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በተመለከከተ "በቁጥር ደረጃ በዝርዝር አልተለየም" ያሉት ኮማንደር ነጋ፤ መረጃው ተሰባሰቦ ሲያልቅ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በክልሉ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ "ፀረ ሠላም" ያሏቸው ኃይሎች ከውጪ አገር ጭምር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃ መገኘቱን ጠቅሰው "ወጣቶችን ለመመልመል እንደሚንቀሳቀሱም" ጨምረው ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከቀናት በፊል መልካን በሚባል ቀበሌ 30 ሰዎችን አፍነው የነበረ ሲሆን አሁን እነሱን መልቀቃቸውን አመልክተው፤ የያዟቸውን ሰዎች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንነታቸው ያልተገጹ ቡድኖች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው ባሻገር በተደጋጋሚ ሰዎችን እያገቱ እንደሚወስዱ ሲዘገብ ቆይቷል።

ይህንንም ለማስቆም የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠርና ድርጊቱን ለማስቆም እየጣሩ መሆኑ ተገልጿል።