የማሊ መፈንቅለ መንግሥት መሪዎቹ የሲቪል መሪ እንዲሰይሙ አንድ ሳምንት ተሰጣቸው

የማሊን ፕሬዚዳንት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ያስወገዱት ወታደራዊው ቡድን ሽግግሩን የሚያሳልጥ አንድ የሲቪል መሪ እንዲሰይሙ የአንድ ሳምንት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

ማሊ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መሪዎች እንዳሉት ቡድኑ የሚያቀርባቸው ሲቪሎች ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት በመሆን አገሪቷን ይመራሉ።

አዲስ ምርጫም እንዲካሄድ ውሳኔ ያስተላልፋሉ ብሏል።

በኒጀሯ መዲና በትናንትናው ዕለት በተካሄደውና ስምንት የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎችን ባሳተፈው ጉባኤ ነው ይህ ጥሪ የቀረበው።

ወታደራዊው ቡድን ለዚህ ጥሪ ምንም ምላሽ አልሰጠም።

ኢኮዋስ ሽግግሩ በአመት ውስጥ መፈፀም አለበት የሚል አስተያየት ቢኖረውም ወታደራዊው ቡድን ግን የስልጣን ርክክቡን ለማካሄድ ምክንያታዊ የሚባል ጊዜ እንደሚያስፈልግ ጠቅሶ ቢያንስ በሁለት አመታት ውስጥ ይፈፀማል ብሏል።

በባለፈው ወር በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን የተወገዱት የማሊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ታመው ለህክምና ወደ አቡዳቢ ሄደዋል።

የ75 አመቱ ፕሬዚዳንት በደም ዝውውር መታወክ (ስትሮክ) ታመው ቅዳሜ ዕለት ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መዲና አቡዳቢ ማቅናታቸውን የአገሪቱ ወታደራዊ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ስልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ወደ ሲቪል አስተዳደር የሚደረገው ሽግግር ላይ ውይይት እያደረጉ ይገኛል።

ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ለተወሰነ ጊዜያትም በወታደራዊ ኃይሉ ቁጥጥር ስር የነበሩ ቢሆንም በኋላ ግን ነፃ ወጥተዋል።

ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ህዝብ የተሳተፈባቸውን የተቃውሞ ሰልፎች መርተዋል።

በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ሙስና፣ የምጣኔ ኃብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ የምርጫ ህግን በተመለከተ ተቃውሞን ከማሰማት ባለፈ የሁሉም መሰረታዊ ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ በመፈንቅለ መንግሥት ወርደዋል።