ናይጄሪያዊያን ከቢግ ብራዘር ለተባረረችው ሴት 100ሺህ ዶላር እያሰባሰቡ ነው

በዝነኛው የናይጄሪያ ቢግ ብራዘር የቲቪ ትዕይንት በጊዜ ለተሰናበተች አንዲት ተወዳዳሪ 100ሺ ዶላር (3.7 ሚሊዮን ብር) እየተሰበሰበላት ነው፡፡

ኤሪካ ብለው ለሚያቆላምጧት ለዚህች ተባራሪ እጩ ገንዘብ የሚዋጣላት አሸናፊ መሆን የነበረባት እሷ ናት በሚል ነው፡፡ አድናቂዎቿ ከውድድሩ መባረሯን አምነው መቀበል ከብዷቸዋል፡፡

እስከአሁን ወደ አስራ አራት ሺህ ዶላር በጎፈንድሚ በኩል ተዋጥቶላታል፡፡ መዋጮው በፍጥነት እየሄደ ነው፡

ኤሪካ ከትናንት በስቲያ እሁድ ነበር ከውድድሩ ውጭ የተደረገችው፡፡ በትእይንቱ ላይ ያልተገባ ባህሪ ታሳያለች ተብሏል፡፡

አብረው ክፍል ለሚጋሯት ተወዳዳሪዎች ክብር የላትም "ምላሰኛ" ናት ብለዋል ድምጽ ሰጪዎች‹‹

ሁለት ተከታታይ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣትም ልታሻሽል ባለመቻሏ ነው ቀይ ካርድ የተሰጣት፡፡

ይህ ግን ወዳጆቿን አሳዝኗል፡፡

መባረሯን ተከትሎ ታማኝ ወዳጆቿ ወዲያውኑ ባሰባሰቡት ገንዘብ 100ሺህ ዶላር ለመስጠት አልመው ተነስተዋል፡፡

የውድድሩ አሸናፊ የሚያገኘው/የምታገኘው ገንዘብ 223ሺ ዶላር ቢሆንም ለሷ ግምሹን ለመስጠት ነው ደጋፊዎቿ ቆርጠው የተነሱት፡፡

ከዚህ ገንዘብ በተጨማሪ አንድ የናይጄሪያ የመኪና አምራች እኔ መኪናና 5ሺ ዶላር እሰጣታለሁ ብሏል፡፡