ትራምፕ በጦር ሜዳ የተገደሉ አሜሪካውያን ወታደሮችን "ተሸናፊዎች" እና "ልፍስፍሶች" አላልኩም አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በግዳጅ ላይ ሳሉ የተገደሉ የአሜሪካ ወታደሮችን ''ተሸናፊዎች'' እና ''ልፍስፍሶች'' ሲሉ ተሳድበዋል መባሉን ተከትሎ በርካቶች በፕሬዝዳንቱ ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

ትራምፕ በግዳጅ ላይ ሳሉ የሞቱ የአሜሪካ ወታደሮችን ''ተሸናፊዎች'' እና ''ልፍስፍሶች' ብለው ጠርተዋል ብሎ የዘገበው 'ዘ አትላንቲክ' የተሰኘው መጽሄት ነበር። ከዚያም 'አሶሺየትድ ፕሬስ' እና 'ፎክስ ኒውስ' ይህን ዘገባ የሚያጠናክሩ ምልከታዎች ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ፕሬዝደንቱ እና አስተዳደራቸው ይህን እንዳላሉ ተናግራዋል።

የአሜሪካ ፖለቲካ ተንታኞች፤ ትራምፕ ሰጡት የተባለው አስተያየት የአሜሪካ ጦር አባላት ቤተሰቦች በቀጣዩ ምርጫ ድጋፍ እንዳይሰጧቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ትራምፕ አሉ የተባለው ምንድነው?

እንደ ዘ አትላንቲክ ዘገባ ከሆነ ትራምፕ እአአ 2018 ላይ በፈረንሳይ የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደሮች መቃብር ስፍራ ለመጎብኘት የነበራቸው እቅድ የተሰረዘው የመቃብር ስፍራው "በተሸናፊዎች የተሞላ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

ዘ አትላንቲክ አራት ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ከሆነ ትራምፕ ወደ ፈረንሳይ የመሄዱን ጉዞ ውድቅ ያደረጉት ዝናቡ ጸጉራቸውን ሊያበለሻሸው ስለሚችል እና በጦርነት የተገደሉ አሜሪካውያንን መዘከር አስፈላጊ ነው ብለው ስለማያምኑ ነው።

በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከጀርመን ጋር ተዋግተው ፈረንሳይ ውስጥ የሞቱ 1800 አሜሪካውያንን ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ልፍስፍሶች" ሲሉ ጠርተዋቸዋል ብሏል ዘ አትላንቲክ በዘገባው። 'ቤሎው ውድ' በተሰኘው የጦር አውድማ የአሜሪካ ወታደሮች የጀርመን ጦር ፓሪስን እንዳይቆጣጠር በከፈሉት መሰዋእትነት ይወደሳሉ።

በወቅቱ ዋይት ሃውስ ትራምፕ ወደ ፈረንሳይ ያልሄዱበት ምክንት የአየር ጸባዩ የፕሬዝደንቱን ሄሊኮፍተር ማንቀሳቀስ ስላላስቻለ ነው ብሎ ነበር።

ዘ አትላንቲክ በዚህ ዘገባው ላይ የምንጮቹን ማንነት አይጥቀስ እንጂ አሶሺየትድ ፕሬስ እና የፎክስ ኒውስ ዘጋቢዋ በዘገባው ከተጠቀሱት መካከል የተወሰኑ እውነታዎችን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።

ከዘገባው በኋላ ምን ተባለ?

በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ የትራምፕ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ጆ ባይደን፤ ትራምፕ አሜሪካንን ለመምራት "ብቁ" አይደሉም ሲሉ ተችተዋል።

"ይህ ዘገባ እውነት ሆኖ የሚገኝ ከሆነ- ከዚህ ቀደም ካለው ነገር በመነሳት እውነት ሊሆን ይችላል- ይህ በጣም አዋራጅ ነው። አሳፋሪ ነው" ብለዋል ጆ ባይደን።

በኢራቅ ግዳጃቸውን ሲወጡ ሁለት እግራቸውን ያጡት ዲሞክራቲኩ ሴናተር ታሚ ዳክዎርዝ፤ "ትራምፕ ለእራሱ ሲል የአሜሪካን ወታደሮች ለመጠቀም ይሞክራል" ብለዋል።

ዘገባው ከወጣ በኋላ ዶናልድ ትራምፕን አጥብቀው ከኮነኑት መካከል የቀድሞ የአሜሪካ ጦር አባላት ይገኙበታል።

'ቮትቬትስ' የሚባለው የቀድሞ ዘማቾች ስብሰብ የሆነው ቡድን፤ ልጆቻቸው በግዳጅ ላይ ሳሉ የተገደሉባቸው ወላጆች ምስክርነትን የያዘ ተንቀሳቃሽ ምስል ይዞ ወጥቷል።

በምስሉ ላይ የሚታዩት ወላጆች፤ "ልጄ ተሸናፊ አይደለም"፣ "ልጄ በኢራቅ የተገደለው አገሩን በኩራት ሲያገለግል ነው"፣ "ልጅን ማጣት ምን ማለት እንደሆነ ዶናልድ ትራምፕ ሊገባው አይችልም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ምን አሉ?

ፕሬዝደንት ትራምፕ ይህን ዘገባ "ሐሰተኛ ዜና" ነው ብለውታል።

ትራምፕ "ማንም ያላደረገውን ለጦር አባላት የደሞዝ ጭማሪ አድርጊያለሁ። ይህን ሁሉ እያደረኩ መስዕዋት ስለሆኑ ጀግኖቻችን እንዲህ አይነት አሉታዊ አስተያየት ልሰጥ አልችልም። ይህ አጸያፊ ዘገባ ነው። አሳፋሪ በሆነ መጽሄት" ብለዋል።

ትራምፕ ትናንት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የዚህ ዘገባ ምንጭ የቀድሞ የዋይት ሐውስ ባልደረባ ጆን ኬሊ ሳይሆን እንደማይቀር ጠቁመዋል። ትራምፕ ጆን ኬሊ የሥራውን ጫና መቋቋም ተስኖት ነበር ብለዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ፣ የመከላከያ ሚንስትሩ ማርክ ኤሰፐር እና የዋይት ሐውስ ባልደረባ ሚክ ሙለቫኔይ ትራምፕ ይህን መሰል አስተያየት እንዳልሰጡ ተከላክለው ተናግረዋል።