ትራምፕ 'ሁለት ሰዎች ገድሏል' የተባለውን ታዳጊ ተከላከሉ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ሞት ያስከተለ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ ደጋፊዎቻቸውን ተከላክለዋል።

ፕሬዝደንቱ፤ በቅርቡ ሁለት ተቃውሞ ሰልፍ ላይ የነበሩት ሰልፈኞችን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረ ታዳጊና ሌሎች ከፀረ-ዘረኝነት ተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር የተጋጩ ሰዎች ራሳቸውን ነው የተከላከሉት ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝደንቱ የመጭው ምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን የግራ ዘመም ተሟቾችን ድርጊት አልወቀሱም ሲል ተችተዋቸዋል።

ጆ ባይደን ከምርጫው በፊት በመራጮች ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት ያላቸው ዕጩ ሆነው እየመሩ ይገኛሉ።

ሰኞ ዕለት በቤተ መንግሥታቸው [ዋይት ሐውስ] መግለጫ የሰጡት ፕሬዝደንት ትራምፕ በዴሞክራት አገረ ገዥዎችና ከንቲባዎች በሚመሩ አካባቢዎች ለተፈጠረው ግርግር ተቃናቃኛቸው ባይደንና ፓርቲያቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።

ሲኤንኤን የተሰኘው ጣቢያ ጋዜጠኛ 'የእርሶ ደጋፊዎች ከተቃዋሚዎች ጋር ተጋጭተው ጉዳት አድርሰዋል፤ ይህንን ይነቅፋሉ ወይ?' ሲል ለፕሬዝደንቱ ጥያቄ ሰንዝሮላቸው ነበር።

በተለይ ፖርትላንድ ግዛት ውስጥ ኦሬጎን ከተማ በሁለቱ ፅንፍ ደጋፊዎች መካከል ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ ነበር። በታዳጊው ተገድለዋል ከተባሉ ሁለት ሰዎች በተጨማሪ የቀኝ ዘመም ርዕዮተ ዓለም ደጋፊ የሆነ ሰው መገደሉ ተነግሯል።

ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝደንቱ "እርግጥ ነው በርካታ ሰዎች ሰልፍ ወጥተዋል፤ ነገር ግን ሰላማዊ ሰልፍ ነበር" ብለዋል።

በዊስኮንሰን ግዛት ኬኖሻ ከተማ አንድ የ17 ዓመት ተጠርጣሪ በመሣሪያ ሁለት ተቃዋሚ ሰልፈኞችት ገድሏል መባሉንስ ይነቅፋሉ ወይ ለትራምፕ የቀረበላቸው ሌላኛው ጥያቄ ነው።

የ17 ዓመቱ ካይል ሪትንሃውስ ሶስት ሰዎችን በጥይት መቷል፤ ሁለቱ ሞተዋል ተብሎ ተጠርጥሯል።

ታዳጊው ይህን ደርጊት የፈፀመው በከተማዋ ጃኮብ ብሌክ የተሰኘ ጥቁር አሜሪካዊ በፖሊስ ሰባት ጊዜ በጥይት መመታቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ሰልፍ ላይ ነው።

ፕሬዝደንቱ ታዳጊውን በተመለከተ ለቀረበላቸው "እሱን እያጣራን ነው" ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"በጣም የሚገርመው እናንተ ያያችሁትን ምስል ነው እኔም ያየሁት። እሱ [ታዳጊው] ከሰልፈኞቹ ለማምለጥ እየሞከረ ነበር፤ ሲመስለኝ እንደዚያ ነው። ከዚያ ሲወድቅ ከበው ጥቃት አደረሰቡት።"

"ጉዳዩ ምርመራ ላይ ነው" ሲሉ ፕሬዝደንቱ ስለታዳጊው ተጠርጣሪ ያላቸውን አስተያየት ቋጭተዋል።

የዴሞክራት ፓርቲ ሰዎች በፕሬዝደንቱ አስተያየት የተሰማቸውን ግርታ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለውና በአዋቂዎች ወንጀል የተጠረጠረው ታዳጊ እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረበም።

ፕሬዝደንት ከጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በኋላ ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ የወጡ አሜሪካውያንን ዘራፈዎች፣ አመፀኞች፣ አጥፊዎች እንዲሁም ወንበዴዎች ሲሉ ነው የሚጠሯቸው።

ተቃናቃኛቸው ጆ ባይደን በቅርቡ በሰልፈኞች መካከል የተፈጠረውን ግጭት አውግዘው ፕሬዝደንት ትራምፕ ሃገሪቱን ሰላም አልባ አድርገዋታል ሲሉ ወቅሰዋል።

የዚህኛው ዙር ተቃውሞ የተቀሰቀሰባት የዊስኮንሰን ግዛት ለሁለቱ ፓርቲዎች ወሳኝ ይዞታ ናት።