አውስትራሊያ: በአንድ ግለሰብ ቤት የተገኙት ሁለት ዘንዶዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአውስትራሊያ ክዊንስላንድ ነዋሪ የሆነው ዳቪድ ታቴ ቤቱ የደረሰው እንደ ሁልጊዜው አገር አማን ነው ብሎ ነበር።

ነገር ግን ሁለት ግዙፍ ዘንዶዎች በቤቱ ጣርያ በኩል በኮርኒስ ውስጥ ሾልከው በመግባት ቀድመውት ቤት ውስጥ ተሰይመዋል።

ዳቪድ ታቴ አንዱን ዘንዶ መኝታ ቤት ውስጥ ሌላኛውን ደግሞ በሳሎኑ ውስጥ ሲያገኛቸው አይኑን ማመን አልቻለም። እያንዳንዳቸው 22 ኪሎ ግራም የሚመዝኑት እነዚህ ዘንዶዎች የዳቪድ ቤት ውስጥ እንግድነት ሳይሰማቸው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ነበር ተብሏል።

እባብና ዘንዶዎችን በማደንና በመያዝ ጥርሱን የነቀለው ስቲቨን ብራውን የእባቦቹን ክብደት ተመልክቶ " አጃኢብ ነው" ብሏል።

ሁለቱ ዘንዶዎች እንዴት ዳቪድ ቤት ሊገኙ ቻሉ ለሚለው እስካሁን ድረስ ያለው መላ ምት ነው።

ከመላ ምቱ አንዱ ሁለቱ ወንድ ዘንዶዎች በሴት ምክንያት እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው እዚህ ቤት ኮርኒስ ውስጥ ደርሰዋል የሚል ነው። ሴቷ ዘንዶ ከወዴት አለች ብሎ ለሚጠይቅ እርሱ ያልተቋጨው የጥያቄው ቁልፍ መልስ ነው።

እነዚህ ዘንዶዎች 2. 8 እና 2.5 ሜትር ያህል ይረዝማሉ።

የቤቱ ባለቤት አቶ ዳቪድ ታቴ ከዚህ ቀደም በቤቴ ጣርያ ላይ እባብ ፀሐይ ሲሞቅ አይቼ አውቃለሁ ብሏል።

" ቤቴ ስመጣ . . . በማዕድ ቤቱ ኮርኒስ ተዘንጥሎ ጠረጴዛው ላይ ወድቋል" ሲል ለካሪየር ሜይል ዘግቧል።

የኮርኒሱን መነደል ያየው ዳቪድ፣ ቤቱን ዞር ዞር ብሎ ሲመለከት ዘንዶውን አገኘው።

ወዲያው ዘንዶ ለሚይዘው ግለሰብ በመደወል ቤቱ ውስጥ የተገኙትን ጥቁር እንግዶች "በፍጥነት እንዲሰናበቱ" ተደርጓል ብሏል።

" በእጄ ንክችም ማድረግ አልፈለኩም" ሲል ለጋዜጣው አስረድቷል።

አቶ ብራውን በሰሜን ብሪዝበን የእባብ ያዢዎችና መላሾች ድርጅት ውስጥ የሚሰራ ሲሆን ለቢቢሲ " እነዚህ ሁለቱ ዘንዶዎች ከዚህ ቀደም ከተለመዱት ግዙፍ እባቦች በተለየ ትልቅ ናቸው" ብሏል።

በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እንደገለፀው ዳቪድ መኖሪያ ቤት እስኪደርስ ድረስ ኮርኒሱን ነድለው መግባታቸውን አላወቀም ነበር።

" አሁን የእባቦች መራብያ ወቅት ነው፤ ስለዚህ እባቦቹ ከተለመደው ጊዜ የተለየ ባህሪ ያሳያሉ፤ የበጋው ሙቀቱ እየጨመረ ስለሚመጣ ፈጣን ይሆናሉ" ብሏል ለቢቢሲ።

ብራውን አክሎ ሰዎች እባብ የሚያጋጥማቸው ከሆነ ባሉበት ቆመው እባቡ እስኪያልፍ ድረስ መታገሥ ብልህነት መሆኑን መክሯል።

" ሁሉም እባቦች አደገኛ ነገር ያዩ በመሰላቸው ወቅት ማምለጥ ነው የሚፈልጉት" ሲል አክሏል።