በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ውጤት እየታየ መሆኑ ተገለጸ

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሲካሄድ በነበረው ድርድር ላይ የተወሰነ ውጤት መታየቱን የኢትዮጵያ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ገለጹ።

ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ እንዳሉት ምንም እንኳን በድርድሩ ውጤቶች እየታዩ ቢሆንም የሚጠበቀውን ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማቅረብ ፍጻሜ ላይ አልደረሰም ብለዋል።

በተጨማሪም የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የሦስቱ አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት አርብ ውይይት መካሄዱንና ባለፉት ቀናት በባለሙያዎች መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር ውጤት ሪፖርት መቅረቡን ገልጿል።

መግለጫው የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ ባለሙያዎች ከነሐሴ 15/2012 ዓ.ም ጀምሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሞላልና የውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ ድርድር ሲያካሂዱ እንደነበር አመልክቶ፤ የዚሁ ውጤት ለአገራቱ ሚኒስትሮቹ ቀርቧል ብሏል።

በሚኒስትሮቹ ስብሰባ ላይም የደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና የአሜሪካ ተወካዮች ታዛቢ ሆነው የተገኙ ሲሆን የአፍሪካ ሕብረት የወከላቸው ባለሙያዎችም እንደነበሩ ተጠቅሷል።

በአገራቱ መካከል እየተካሄደ ያለውን ድርድር ቀጣይ ሂደት በተመለከተም ለደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀ መንበር በደብዳቤ ለማሳወቅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የዚህ የሦስቱ አገራት ድርድር ሂደት ከሱዳን በኩል የሚሰጥ ማረጋገጫን መሰረት በማድረግ መስከረም 04/2012 ዓ.ም እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በቢሊየን ዶላሮች አውጥታ እየገነባችው ባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር በተለያዩ ጊዜያት ለመካሄድ የቻለ ቢሆንም ያለመቋጫ ሲቋረጥ መቆየቱ ይታወሳል።

በተለይ በግድቡ የውሃ አሞላልና አጠቃላይ የሥራ ሂደትን በተመለከተ አገራቱ ለመስማማት ተቸግረው የቆዩ ሲሆን በተለይ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ለመጀመር የነበራትን ዕቅድ ካሳወቀች በኋላ ለመስማማት አዳጋች ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።

ነገር ግን ኢትዮጵያ በነበረው ከፍተኛ የክረምት የዝናብ መጠን ታግዛ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ዕቅዷን ማሳካቷን ካሳወቀች በኋላ በቀሪ ጉዳዮች ላይ ድርድሩ ቀጥሏል።