ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመን፡ 1 ሺህ 200 ኢትዮጵያውያንን ከየመን ለማውጣት እየተሰራ ነው-የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያ መንግሥት በየመን በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ 1200 ኢትዮጵያውያንን ሊያስወጣ መሆኑን ገለፁ።
ቃል አቀባዩ ይህንን ያሉት በውጪ አገር ስለሚገኙ ኢትዮጵያ እና ስለ ሕዳሴው ግድብ በዛሬው እለት በመሥሪያ ቤታቸው መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሊባኖስ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሲናገሩ 180 ኢትዮጵያኖችን ወደ አገር ውስጥ ለመመለስ ሰነድ መዘጋጀቱንና ዜጎችም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በየመን ባለው የፀጥታ ችግር ምከንያት ኢትዮጵያኖችን በአንድ ስፍራ ሰብስቦ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።
ይኹን እንጂ ከአውሮጳ ሕብረት ተወካዮች ጋር በመሆን 1200 ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች እየተመቻቹ መሆኑን አስታውቀዋል።
"ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር መልካም መግባባትና ግንኙነት አለን" ያሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና፣ ከየመን ወደ ሳዑዲ አቋርጠው የገቡ ኢትዮጵያኖች በሳዑዲ መንግሥት ጥበቃ የሚደረግበት ስምምነት እንዳለም አስረድተዋል።
በቅርቡ ሂይውማን ራይትስ ዎች ያወጣውን ሪፖርት በመጥቀስ በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ዲና ሲመልሱ "እንዲህ አይነት ችግር የለም ማለት ይከብዳል፤ ይሁን እንጂ በሳዑዲ ያሉት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ለኢትዮጵያውያን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ትዕዛዝ ተላልፏል" ብለዋል።
ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሚያደርጉት ድርድር እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።
" እኛ በፍላጎት፣ በእምነት እና በአንድ ልብ ሆነን ውይይቱን እየተሳተፍን እንገኛለን ውጤቱንም የምናሳውቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።
አምባሳደር ዲና አክለውም ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት ወክለው የሚሰሩ አምባሳደሮች ዓመታዊ ስብሰባቸውን የፊታችን ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚሰበሰቡ ተናግረዋል።