ኬንያ በሊባኖስ በቆንስላዋ በደል ስለሚፈጸምባቸው ዜጎቿ ምርመራ ልታደርግ ነው

ኬንያ በሊባኖስ በሚገኙ ዜጎቿ ላይ የደረሰውን ማንገላታት የሚያጣራ ቡድን ወደ መካከለኛው ምሥራቋ አገር ልትልክ ነው።

ኬንያውያን በቤይሩት ቆንስላ ውስጥ መንገላታት እንደደረሰባቸው የሚያሳይ ዘገባ የቀረበው በሲኤንኤን ነው።

የሴኤንኤን የምርመራ ዘገባ በሊባኖስ በቤት ሠራተኝነት የሚሰሩ ኬንያውያን በአገራቸው ቆንስላ ባለስልጣን እና ረዳቱ የሚደርስባቸውን ብዝበዛ ወይንም ጥቃት ይዞ ቀርቧል።

በዚህ የሲኤንኤን ዘገባ ላይ በርካቶች የተጠየቁ ሲሆን እንደሚመቱ፣ እንደሚሰደቡና እንደሚዘለፉ፤ ለቆንስላው አገልግሎት ከተገቢው በላይ ክፍያ እንደሚጠየቁ እንዲሁም ወደ አገራቸው ለመመለሻ የሚሆን ገንዘብ እንዲያገኙ በወሲብ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ እንደሚመክሯቸው ጠቅሰው አስረድተዋል።

የጉዳዮን እውነትነት አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትም እማኝነቱን በመስጠት አረጋግጧል።

ነገር ግን የቆንስላው ባለስልጣናት ሁለቱም ሊባኖሳዊያን ሲሆኑ፤ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

የኬንያ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ በኩዌት የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ፣ በሊባኖስ የሚገኘውን ቆንስላ በኃላፊነት የሚመራ በመሆኑ ወደ ቤሩት በመጓዝ ጉዳዩን ያጣራል ብለዋል።

በኩዌት የኬንያ አምባሳደር ሃሊማ ሞሐመድ ለዴይሊ ኔሽን "በአሁኑ ሰዓት በረራ ዝግ በመሆኑ በሚቀጥለው ሳምንት ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ሊባኖስ ለመጓዝ አቅደናል" ብለዋል።

በቅርቡ በሌባኖስ ውሰጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመባባሱ እና በምጣኔ ሃብቱ ድቀት የተነሳ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን በቆንስላቸው በር ላይ አሰሪዎቻቸው ጥለዋቸው መሄዳቸው ይታወሳል።