ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ምርጫ፡ ጆ ባይደን ዶናልድ ትራምፕን እንዲገዳደሩ በይፋ ተመረጡ
የቀድሞው የባራክ ኦባማ ምክትል ጆ ባይደን በይፋ የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ሆነው ተመረጡ፡፡
ምርጫው የተካሄደው በፓርቲው ታላቅ ጉባኤ ነው፡፡
በአሜሪካ የፓርቲዎች አሰራር ባሕል እጩው ቀደም ብሎ ቢታወቅም ይፋዊ ውክልና የሚሰጠው በጠቅላላ ጉባኤ ነው፡፡
በዚህ የማጠቃለያ ጉባኤ ላይ ሥመ ጥር ሰዎች፣ የፓርቲ መሪዎች፣ የቀድሞ የአገር ግዛት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች ተገኝተዋል፡፡
በጉባኤው ላይ ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው ሁለቱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መገኘታቸው ነው፡፡ ቢል ክሊንተንና ጂሚ ካርተር እንዲሁም የቀደውሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፖል ጉባኤውን አድምቀውታል፡፡
ኮሊን ፖል ሪፐብሊካን ቢሆኑም በዶናልድ ትራምፕ ደስተኛ ባለመሆናቸው ለጆ ባይደን ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቢል ክሊንተን በጉባኤው እንደተናገሩት ‹‹ዶናልድ ትራምፕ ታላቋን አሜሪካንን ቀውስ ውስጥ ከቷታል››፡፡
በኅዳሩ ምርጫ ከሕዝብ የተሰበሰበ ቅድመ አስተያየት ትንበያ (opinion polls) ጆ ባይደን ትራምፕን በትንሽ ልዩነት መምራት ጀምረዋል፡፡
በ50ዎቹም ግዛቶች የሚገኙ የፓርቲ ወኪሎች (ዴሊገትስ) በሰጡት ድምጽ መሰረት ነው ጆ ባይደን በይፋ የትራምፕ ቀጣይ ተገዳዳሪ ሆነው የተመረጡት፡፡
ጆ ባይደን በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ በትንሹ ለ30 ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ነጩ ቤተ መንግሥት ለመግባት ሲፎካከሩም ይህ ለ3ኛ ጊዜ ነው፡፡
የ77 ዓመቱ ባይደን በዲሞክራቲክ ምርጫ መጀመርያ ላይ በሳንደርሰን ተበልጠው ስለነበር ተስፋ እንደሌላቸው ታስቦ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ማርሽ ቀይረው ለዚህ በቅተዋል፡፡
ይህ የፓርቲ ታላቁ ጉባኤን ልዩ የሚያደርገው በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በቪዲዮ ስብሰባ መደረጉ ነው፡፡
በጉባኤው ላይ የአምስት ደቂቃ ንግግር ያደረጉት ቢል ክሊንተን ትራምፕን ክፉኛ ተችተዋቸዋል፡፡ ቢል ንግግራቸውን ያደረጉት ኒውዮርክ ከሚገኘው ቤታቸው ሆነው ነው፡፡
ሪፐብሊካኑ ፖል በበኩላቸው ዶናልድ ትረምፕ ቀጣፊ መሪ ናቸው ሲሉ ለጆ ባይደን ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ኮሊን ፖል በጆርጅ ቡሽ ጊዜ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡
የሟቹ የሴናተር ጆን ማኬይን ባለቤት የነበሩት ሲንዲ ማኬይን ለጆ ባይደን ድጋፍ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪ የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስር ጆን ኬሪ፣ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ተወዳጇ ሚሼል ኦባማ የድጋፍ ንግግሮችን አሰምተዋል፡፡
የዲሞክራቶች ታላቅ ጉባኤ ዛሬና ነገም ይቀጥላል፡፡ ካሚላ ሐሪስ፣ ሂላሪ ክሊንተንና ባራክ ኦባማ የሚያደርጓቸው ንግግሮች በጉጉት ይጠበቃሉ፡፡