ኮሮናቫይረስ ፡ ኮቪድ-19 በየትኞቹ የዓለም አገራት ላይ በርትቷል?

ጭምብል ያደረጉ ሴቶች በመንገድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኮሮናቫይረስ በቻይናዋ ዉሃን መነሳቱ ከተሰማ ወዲህ ከግማሽ ዓመት በላይ ሆኖታል። እስካሁንም ከ21 ሚሊየን በላይ ሰዎች በአጠቃላይ መያዛቸው ሲረጋገጥ ቫይረሱ 188 የዓለም አገራትን አዳርሷል።

ከ765 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ ከዚሁ ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።

በበርካታ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሁንም በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የወረርሽኙን ስርጭት ስኬታማ ሊባል በሚችል መልኩ እየተቆጣጠሩት ይገኛሉ።

በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት ደግሞ የላቲን አሜሪካ አገራት የቫይረሱ ዋነኛ ማዕከል ሆነዋል።

ብራዚል እስካሁን ከ100 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሞተውባት ከአሜሪካ በመቀጠል ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሌላኛዋ አገር ሜክሲኮ ደግሞ በኮቪድ-19 ሳቢያ የሞቱባት ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺ በላይ መሆኑን አስታውቃለች።

በተጨማሪም እንደ ኮሎምቢያ፣ ፔሩ፣አርጀንቲና እና ቬንዙዌላ የመሳሰሉ አገራትም በቫይረሱ ክፉኛ ተጠቅተዋል።

ከላቲን አሜሪካ ውጪ ደግሞ ኢራን የቫይረሱን ጉዳት መቋቋም ካልቻሉት መካከል ትጠቀሳለች። መንግሥታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገሪቱ ስርጭቱ እንደ አዲስ እያገረሸ ሲሆን 20 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል።

ነገር ግን የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ እንዳጋለጠው በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር መንግሥት ከሚናገረውም በላይ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።

ኮቪድ-19 የበረታባቸው

በአፍሪካ ደቡብ አፍሪካና ግብጽ እስካሁን በአህጉሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግበዋል።በዚህም ምክንያት ደቡብ አፍሪካ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከ500 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በማስመዝገብ በዓለማችን ከተዘረዘሩት ሰባት አገራት ተርታ ተቀምጣለች።

እንደ አጠቃላይ በአህጉሪቱ ግን እስካሁን ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን እያደረሰ ያለው ጉዳትና ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት መጠን እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ሕንድ ደግሞ በዓለማችን ከፍተኛውን በአንድ ቀን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አስመዝግባለች።

እስካሁንም 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ያረጋገጠች ሲሆን በየቀኑ ደግሞ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ይያዙባታል። ይህ ቁጥር ደግሞ በዓለማችን እስካሁን ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከቻይና በመቀጠል ከፍተኛውን የዓለም ህዝብ ቁጥር የያዘችው ሕንድ በአጠቃላይ በሟቾች ቁጥር አራተኛ ናት። ነገር ግን አሁንም ቢሆን አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደቡን ማላላቷን ቀጥላበታለች።

የአውሮፓ አገራትም ቢሆኑ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ተስኗቸዋል።

ስፔን በወረርሽኙ የመጀመሪያ ወራት ክፉኛ ተጠቅታ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በቅርብ ሳምንታት ደግሞ ቫይረሱ እንደ አዲስ እያገረሸ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።

ፈረንሳይም ብትሆን መጋቢት ወር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችና የሟቾች ቁጥር አስመዝግባለች። ነገር ግን ከሚያዝያ በኋላ በወሰደቻቸው እርምጃዎች ከፍተኛ የነበረውን የስርጭት መጠን መቀነስ ችላለች።

በአሜሪካ ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት እንደ አዲስ ካገረሸ በኋላ አሁን ላይ ትንሽ መቀነስ እያሳየ ነው። እስካሁን በአጠቃላይ በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ወደ 170 ሺ የተጠጋ ሲሆን ይህም ከዓለም አንድ አምስተኛውን ቁጥር እንድትይዝ አድርጓታል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ''ካልደፈረሰ አይጠራም'' በማለት ነገሮች ከዚህም በላይ ሊከፉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ እንደተነበየው ከሆነ የፊታችን ታህሳስ ወር ላይ በአሜሪካ በቫይረሱ ሳቢያ ብቻ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ295 ሺ በላይ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ዩኒቨርሲቲው አክሎም ከ90 በመቶ በላይ አሜሪካውያን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያደርጉ ከሆነ ግን ቁጥሩን ወደ 230 ሺ ዝቅ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁሟል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተጽእኖ አሳድሯል። ከሚያዝያ ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ብቻ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 33 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

በአጠቃላይ በአለም ላይ ያለው ቁጥር ምን ይመስላል?

እስካሁን ድረስ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 21 ሚሊዮን አካባቢ ሲሆን ከ765 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም ሲናገሩ ''በቀላሉ ለመግለጽ ወረርሽኙ ከዚህ በፊት ከነበሩት የከፋና አስቸጋሪ ዓለማቀፍ የጤና እክል ነው ካሉ በኋላ ድርጅቱ እንዲህ አይነት ፈተና ገጥሞት አያውቅም ''ብለዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም የቫይረሱ ስርጭት በ188 አገራት እንደደረሰም አስታውሰዋል። እናም በዓለማችን ላይ በበቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በአሜሪካ፣ ብራዚል እና ሕንድ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ አገራት መንግሥታት ስርጭቱን ለመቆጣጠር ይበጀናል ያሏቸውን እርምጃዎች በሙሉ በመውሰድ ላይ ናቸው። አንዳንዶች አሁነም የእንቅስቃሴ ገደቡን ማላለት ተገቢ አይደለም ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ኢኮኖሚያችን ከሚደቅ ጠንቀቅ እያልን የንግድ ተቋማትን መክፈት አለብን እያሉ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳስታወቀው በያዝነው ዓመት መጨረሻ አካባቢ በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ እስከ 265 ሚሊየን የሚደርሱ የዓለማችን ዜጎች የምግብ እጥረትና ረሀብ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ኮሮና
Banner