ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊባኖስ፡ የቤይሩት ፍንዳታን ተከትሎ በርካታ የህክምና ማዕከላት ጥቅም አልባ ሆነዋል
ባለፈው ሳምንት በቤይሩት ከፍተኛ የሚባለውን ፍንዳታ ተከትሎ የጤና ማዕከላት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል ተብሏል።
የአለም ጤና ድርጅት በከተማዋ አደረግኩት ባለው ግምገማ ከ55ቱ ውስጥ ግማሹ ጥቅም አልባ መሆናቸውን ተረድቷል።
ትልልቅ የሚባሉ ሶስት ሆስፒታሎች የተዘጉ ሲሆን ተጨማሪ ሌሎች ሶስት ሆስፒታሎች ደግሞ የሰራተኞቻቸውን ቁጥር ቀንሰዋል።
የድርጅቱ አሰሳ እንደጠቆመው በጤና ማዕከላቱ ውስጥም የኮሮናቫይረስን ለመግታት የወጡ መመሪያዎች ተግባራዊ እየሆኑ አይደለም።
ቤይሩትን ባንቀጠቀጣት በዚህ ፍንዳታ 200 ዜጎቿን ያጣች ሲሆን 6 ሺህ ያህል ደግሞ መጎዳታቸውንም የከተማዋ አስተዳዳሪ ማርዋን አቡድ አስታውቀዋል።
ለፍንዳታው ምክንያት ደግሞ በስፋት ለግብርና ማዳበሪያነት የሚውለው የአሞኒየም ናይትሬት ኬሚካል በወደብ አካባቢ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ በመቀመጡ ነው። ከፍተኛ ክምችት የተባለው ይህ ኬሚካል ወደ 2 ሺህ 700 ቶንም ይመዝናል።
ፍንዳታው ሳምንቱን በትናንትናው ዕለት የደፈነ ሲሆን ይህን ያህል ተቀጣጣይ ኬሚካል ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ በወደብ ላይ መቀመጡ ቁጣን ቀስቅሷል። ይህ የገነፈለው ቁጣም የሊባኖስ መሪን ከስልጣናቸው እንዲለቁ አድርጓቸዋል።
የሆስፒታሎቹ ሁኔታ እንዴት ነው?
በምስራቅ ሜድትራንያን የአለም ጤና ድርጅት ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ዶክተር ብሬናንን በቤይሩት የሚገኙ 55 ዋነኛ የጤና ማዕከላትን ሁኔታ ገምግመዋል።
ከነዚህም ውስጥ ግማሹ ጥቅም አልባ የሆኑ ሲሆን በዚህም ምክንያት በአገሪቷ 500 ለህሙማን የሚሆኑ አልጋዎችን እጥረት አስከትሏል።
ሆስፒታሎቹ በፍንዳታው በተጎዱ ሰዎች በመጨናነቃቸው ሌሎች ህመምተኞችን ማከም አልቻሉም ብለዋል።
የአለም ጤና ድርጅትም የተዘጉት ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችን መክፈትና አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ መሆን እንዳለበት እያሳሰበ ነው።
ድርጅቱ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ለሚያስፈልጋቸው የጤና ማዕከላትም እያሰራጨ ይገኛል።
የኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት ሊባኖስ የጤና ማዕከላቱ ከጥቅም ውጭ መሆን ራስ ምታት ሆኖባታል።
በቫይረሱ 7 ሺህ 121 ሰዎች መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 87 ሰዎችም ህይወታቸው ማለፉን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ሊባኖስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች የነበረውን ጥረት ያመሰገኑት ዶክተር ብሬናን ፍንዳታውን ተከትሎ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች መጨመሩ ስጋት አጥሏል ብለዋል።
አገሪቷም ከፍተኛ የሚባለውን ቁጥር የመዘገበችው በዚህ ሳምንት ሲሆን ዳይሬክተሩ ከፍተኛ ጥንቃቄና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግም አሳሳስበዋል።
ፍንዳታው ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለባት ቤይሩት ታሪካዊ ቦታዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህንፃዎች ፈራርሰዋል። ከተማዋን የጦር አውድማ አስመስለዋታል።