ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ሪፐብሊካኖች በሚያደርጉት እጩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሚዲያዎች እንዳይሳተፉ ተወሰነ
የአሜሪካ የሪፐብሊካን ፓርቲ በዚህ ወር እጩ ፕሬዚዳንቱን በይፋ ለመምረጥ እቅድ ይዟል። ይህ ምርጫም ሚዲያዎች እንዳይሳተፉበትና በዝግም እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የሪፐብሊካን ቃለ አቀባይ እንደተናገሩት ሚዲያ እንዳይሳተፍ የተወሰነው ከኮሮናቫይረስ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ መሆኑንም አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
በሰሜን ካሮላይና የሪፐብሊካን ልዑካን ተሰባስበውም እጩ ፕሬዚዳንቱን ዶናልድ ትራምፕን በይፋ እንደገና ይመርጣሉ።
336 የሚሆኑ ልዑካን በሰሜን ካሮላይና ግዛት፣ ቻርሎቴ ከተማ በዚህ ወር ይሰባሰባሉ።
እነዚህ ልዑካን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቁጥሩ በመገደቡ መገኘት ያልቻሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ አባላትን ወክለው ይገኛሉ።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፓርቲያቸው ብቸኛ እጩ ተወዳዳሪ ሲሆኑ፤ እንደገና በይፋ መመረጣቸውም የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸውንም እንዲሁ በይፋ መጀመሩን የሚያበስር ነው ተብሏል።
"ፓርቲያችን በፌደራል እንዲሁም በተለያዩ ግዛቶች የወጡ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን በመከተልም ነው ስብሰባውን የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥርን የወሰንነው" በማለት ቃለ አቀባይዋ ተናግረዋል።
ይህ ውሳኔ ከዚህ በፊት ይደረጉ የነበሩ ስብሰባዎቸን አካሄድ የቀየረ ነው ተብሏል። ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነቱ ስብሰባ የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ የሚስብና ለህዝቡም መልዕክቶች ይፋ የሚሆኑበት ነበር።
የሰሜን ካሮላይና አስተዳዳሪ በሚገኙት ሰዎች ብዛትና አካላዊ ርቀት ጋር ተያይዞ ስብሰባውን ወደ ሌላ ቦታ እንዲያደርጉት መጠየቀቻውን ተከትሎ ግንቦት ወር ላይ ወደ ጃክሰን፣ ፎሎሪዳ እንደሚደረግ ትራምፕ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ወደ በኋላ ፍሎሪዳ ሊደረግ የነበረውን ስብሰባ በመሰረዝ ወደቀደመው እቅድ በመመለስ ሰሜን ካሮላይና እንዲካሄድ ተወስኗል።ግዛቲቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ያለምክንያት እያቀጣጠሉ ነው በማለት ወንጅለዋል።