ኮሮናቫይረስ፡ የህሙማን ቁጥር ከሆስፒታሎች አቅም እንዳያልፍ የሰጋችው ከተማ

ካሪ ላም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሆንክ ኮንግ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየናረ ይገኛል። የከተማዋ መሪ ካሪ ላም፤ የህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የሆስፒታሎችን አቅም “ሊያንኮታኩት ይችላል” ብለዋል።

በከተማዋ የበሽታው ማሕበረሰባዊ ስርጭት ጫፍ ላይ እየደረሰ መምጣቱን መሪዋ ተናግረዋል። ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡም አሳስበዋል።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ግዴታ ሆኗል። ምግብ ቤቶች መስተንግዶ እንዲያቆሙም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

ኮቪድ-19 መሰራጨት በጀመረባቸው ወራት ሆንክ ኮንግ በሽታውን በመቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ነበረች። አሁን ግን በየቀኑ ከ100 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እየተነገረ ነው።

ከአንድ ወር በፊት በ24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ከዓሥር በታች ነበሩ።

ካሪ ላም ምን አሉ?

መሪዋ ካሪ ላም ትላንት በሰጡት መግለጫ፤ የሆንክ ኮንግ ማሕበረሰብ ውስጥ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭበት ነጥብ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ይህም የጤና ሥርዓቱን እንደሚያቃውሰው፣ በተለይም የአረጋውያን ሕይወት እንደሚቀጠፍም ተሰግቷል።

መሪዋ ነዋሪዎች አካላዊ ርቀት እንዲጠብቁና በተቻለው መጠን ከቤት እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ካሪ ላም መግለጫ ከመስጠታቸው ቀደም ብሎ ሆንግ ኮንግ ውስጥ በ24 ሰዓት 106 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። በአንድ ቀን 23 ሰዎችም ሞተዋል።

ምን ውሳኔ ተላለፈ?

ከዛሬ ጀምሮ ምግብ ቤቶች መስተንግዶ እንዳይሰጡ ታግደዋል። በተጨማሪም ከአንድ ቤተሰብ ውጪ የሆኑ ሰዎች ሲገናኙ፤ ቁጥራቸው ከሁለት መብለጥ የለበትም።

በዚህ ወር መባቻ ላይ እስከ 50 ሰዎች መሰብሰብ ይችሉ ነበር። ከዛም ቁጥሩ ወደ አራት አሁን ደግሞ ወደ ሁለት ተቀንሷል።

ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ነው። መጠጥ ቤቶች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያዎችና የውበት ሳሎኖችም ይዘጋሉ ተብሏል።

ሆንክ ኮንግ እስከዛሬ ከወሰደቻቸው እርምጃዎች የአሁኑ ጥብቁ ነው።

ሆንክ ኮንግ ቫይረሱን መቆጣጠር ችላ ነበር?

ቫይረሱ መሰራጨት በጀመረበት ወቅት ሆንክ ኮንግ በሽታውን መቆጣጠር ችላ ነበር።

ወደ ቻይና ከተሞች የሚካሄዱ ጉዞች ተቀንሰው፣ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው በፍጥነት የሚለዩበት አሠራር ተዘርግቶ ነበር።

ከተማዋ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ሳይገኝ ሳምንታት ያለፉበት ወርም ነበር።

ነገር ግን ሰዎች ወደ ቀደሞው አኗኗራቸው መመለስ ሲጀምሩ፤ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨመረ።

በየቀኑ በቫይረሱ የተያዙ ከዓሥር በታች ሰዎች ሪፖርት ሲደረግ ቢቆይም አሁን ግን ቁጥሩ 120 ደርሷል።

በሆንክ ኮንግ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩ ፕ/ር ጂን ዶንግያን እንዳሉት፤ ድንበር አካባቢ ተገቢው ቁጥጥር አለመደረጉ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

“ቫይረሱን በማሕበረሰቡ ውስጥ እያሰራጩ የሚገኙት በበሽታው ተይዘው ወደ ሆንክ ኮንግ የገቡ የሌሎች አገራት ዜጎች ሊሆኑ የይችላሉ” ብለዋል።

የቫይረሱ ስርጭት መባባስ ሆንክ ኮንግን እንደሚጎዳት ሳይንቲስቶች ተናግረዋል።

ቫይረሱ ቢያንስ ለ22 ቀናት ሳይስፋፋ ቆይቶ እንደነበረ በመጥቀስ፤ ቫይረሱ ከሰዎች ጋር እንደተላመደና ይህም በቀላሉ እንዲሰራጭ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ምርጫ ይካሄዳል?

አዲሶቹ የኮሮናቫይረስ መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎች የተወሰዱት የሆንክ ኮንግ ምክር ቤት ምርጫ በአንድ ዓመት በተገፋበት ወቅት ነው።

የሆንክ ኮንግ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት፤ መንግሥት በከሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ገና ውሳኔውን በይፋ አልገለጸም።

ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው መስከረም 6 ነበር።

ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ ምርጫው የተራዘመው አዲሱን የብሔራዊ ደህንነት ሕግ በተመለከተ የተነሳውን ቁጣ ለማርገብ ነው ይላሉ።

ኮሮና
Banner