ሃሪ እና ሜጋን ልጃቸውን በድሮን ፎቶ ያነሳው ግለሰብ ላይ ክስ መሰረቱ

የሰሴክሱ መስፍን ሃሪ እና ባለቤቱ ሜጋን በድሮን አማካኝነት ጨቅላ ልጃቸው አርቺን ፎቶ ያነሳው ግለሰብ ላይ ክስ መሰረቱ።

በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ የተከፈተው ክስ፤ በስም ያልተጠቀሰው ግለሰብ የ14 ወራት ጨቅላ የሆነውን የሃሪ እና ሜጋን ልጅ አርቺን በመኖሪያ ቤታቸው በድሮን አማካኝነት ፎቶግራፍ አንስቷል ይላል።

ጥንዶቹ ፎቶግራፎቹ የተነሱት የልጃቸውን እና የእነሱን ግላዊነት በተላለፈ መልኩ ነው ይላሉ።

ሃሪ እና ሜጋን ከዚህ ቀደም በድብቅ ፎቶ የሚያነሷቸውን ሰዎች አስጠንቅቀው ነበር።

ሜጋን፤ ካናዳ ውስጥ ልጇኝ ከፊት አዝላ ሁለት ውሾች በገመድ እያንሸራሸረች የምትታይበት ፎቶ ሾልኮ ከወጣ በኋላ ነበር ጥንዶቹ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክታቸውን ያሰሙት።

ሃሪ እና ሜጋን ከወራት በፊት ከእንግሊዝ ንጉሳዊያን ስርዓት እራሳቸውን ማግለላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን መቀመጫቸውን በአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ አድርገዋል።

የጥንዶቹ ጠበቃ የሆኑት ማይክል ኩምፕ፤ “በካሊፎርኒያ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባላት በመኖሪያ ቤታቸው የግላዊነት መብታቸው የተጠበቀ ነው። ድሮንም፣ ሄሊኮፍተር ወይም ፎቶግራፎች ይህን መብት መተላለፍ አይችሉም” ብለዋል።

ጠበቃው ጨምረው እንደተናገሩት፤ ሃሪ እና ሜጋን በተደጋጋሚ ፎቶግራፍ ተደብቀው በሚያነሱ ፓፓራዚዎች ምክንያት ግላዊ መብታቸው በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነው።

በመኖሪያ ቤታቸው ላይም ሄሊኮፍተር ፎቶግራፍ ለማንሳት በተደጋጋሚ እንደሚበር እና ፎቶግራፍ አንሺዎችም አጥራቸውን እየሰረሰሩ ፎቶግራፍ ማንሻ ሌንሶችን አስርገው እንደሚያስገቡ ጠበቃው ተናግረዋል።

የልዑል ሃሪ እናት የሆነችው ልዕልት ዳያና በሞተርብስክሌት ሲከታተሏት ከነበሩ 'ፓፓራዚዎች' ስታመልጥ ሳለች ባጋጠማት የመኪና አደጋ ህይወቷ ማለፉ አይዘነጋም።