"ሴት ምንም ብትማር፤ ባል የሚስት ራስ ነው" ያሉት ፓስተር ክፉኛ እየተተቹ ነው

ናይጄሪያዊው ፓስተር ኢኖች አደቦይ ከሰሞኑ በትዊተር ላይ መነጋገሪያ ከሆኑ ሰዎች መካከል ግንባር ቀደም ሆነዋል። ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ከ34 ሺህ ጊዜ በላይ በትዊተር ላይ ስማቸው ተጠቅሷል።

ይህ የሆነው ፓስተሩ በኢንስታግራም ገፃቸው ላይ ከ50 ዓመታት በላይ የትዳር አጋራቸውን ፎሉኬ ልደትን በማስመልከት ያጋሩትን ፅሁፍ ተከትሎ ነው።

ፅሁፉ "ዛሬ የባለቤቴ ልደት ነው፤ በተለይ አዲስ ተጋቢዎች ከእርሷ ብዙ ነገር ሊማሩ ይገባል። በጣም ጠንካራ ሴት ናት . . . " ሲል ይጀምራል።

ከዚያም "እቅዷ ምንም ይሁን ምን ከእርሷ ጋር የሆነ ቦታ መሄድ እንደምፈልግ ከነገርኳት፤ ስትሰራው የነበረውን ነገር ሁሉ ጥላ ከእኔ ጋር ትመጣለች" ይላሉ።

አገልጋዩ በዚህ ብቻ አላበቁም "ሴቶች ምንም ያክል ቢማሩና ስኬታማ ቢሆኑ ባል የሚስት ራስ ነው፤ በመሆኑም ሁል ጊዜም ባልን ማክበር አለባችሁ" ሲሉም ዘለግ ባለው ፅሁፋቸው አትተዋል።

ይህንን ፅሁፍ በርካቶች የሴቶችን መብት የሚፃረር ሲሉ በትዊተር ላይ ተቃውመውታል።

በርካታ ሰዎችም ቃላቶቹን 'አስቀያሚ' ሲሉ በመጥራት ፓስተሩ ላይ ትችት ሰንዝረዋል። የባለቤታቸውን የልደት በዓልም በእርሷ ላይ ያለውን የበላይነት ለማሳየት መጠቀም አልነበረባቸውም ሲሉም ወቅሰዋል።

በሌላ በኩልም ለአምስት አስርት ዓመታት የዘለቀውን ትዳራቸውንም ያወደሱ አልጠፉም። አንዲት ሴት የሌላውን ሰው የበላይነት አውቃ ከተቀበለች ምን ችግር አለው፤ ሁለት ካፒቴኖች አንድ መርከብ አይዘውሩም ሲሉ ለጥንዶቹ ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።