በአሜሪካ ከማስክ አጠቃቀም ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የሰው ህይወት ጠፋ

በአሜሪካዋ ሚሺጋን ግዛት ከፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም ጋር በተፈጠረ አለመግባባት አንድን ግለሰብ በስለት ወግቶ የተሰወረን ግለሰብ ፖሊስ በጥይት መትቶ ገድሏል።

ክስተቱ የተፈጠረው በአንድ መገበያያ መደብር ውስጥ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

ሼን ሩዊስ የተባለው ግለሰብ በመደብሩ ውስጥ የፊት እና አፍ መሸፈኛ ማስክ ሳያደርግ እየተገበያየ ሳለ አንድ የ77 ዓመት አዛውንት ማስክ ማድረግ እንዳለበት ይገዳደሩት ጀመር።

በሁለቱ ግለሰቦች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተባብሶ ሼን ሩዊስ የ77 ዓመቱን አዛውንት በስለት ወግቶ ከአካባቢው ለማምለጥ መሞከሩን ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ ሩዊስ ሲያሽከርክር የነበረውን መኪና ሲከታተል ቆይቶ፤ የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመበት ስፍራ 10 ኪ.ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ በአንድ ሴት የፖሊስ ባልደረባ እንዲቆም ይታዘዛል።

ተጠርጣሪው ከመኪናው ከወረደ በኋላ በኃይል እና በፍጥነት ወደ ፖሊስ አባሏ ሲጠጋ፤ የፖሊስ አባሏ በጥይት ተኩሳ መታዋለች። ፖሊስ ይህን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ አድርጓል።

ሼን ሩዊስ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ ግን ሊተርፍ እንዳልቻለ ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ እንደሚለው የ43 ዓመቱ ሩሲስ የጦር መሳሪያ ይዞ ነበር።

በስለት የተወጉት የ77 ዓመቱ አዛውንት በሆስፒታል በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

በአሜሪካ የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ መሰል አደጋዎች ሲያጋጥሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከአንድ ሳምንት በፊት አንድ የመደብር ጠባቂ የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርግ ወደ መደብሩ የገባን ደንበኛ በጥይት መትቶ ገድሏል።