የአሜሪካ ፌደራል መንግሥት ከ17 ዓመታት በኋላ የሞት ቅጣት ሊያስፈጽም ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔን ተከትሎ በአሜሪካ ከ17 ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረው በፌደራል መንግሥቱ ተግባራዊ የሚደረግ የሞት ፍርድ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ኢንዲያና ግዛት ውስጥ ሊፈጸም ነው።
በግድያ ወንጀል ሞት የተፈረደበት ዳንኤል ልዊስ የተባለው ፍርደኛ ባለፈው አርብ ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይረግበት በአንድ የፌደራል ዳኛ እግድ ተላልፎበት ነበር።
ለዚህም የተሰጠው ምክንያት የሟቾች ቤተሰቦች ውሳኔው ተግባራዊ ሲሆን ለመገኘት ቢፈልጉም በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት መገኘት ስለማንችል ለሌላ ጊዜ ይዘዋወርልን በማለታቸው ነበር።
ነገር ግን መንግሥት ይግባኝ ጠይቆ ውሳኔው እንዲቀለበስ የሚያደርግ ሕጋዊ ትዕዛዝ በማግኘቱ ብይኑ ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል።
በአገሪቱ የሟች ቤተሰቦች በገዳይ ላይ የሞት ፍርዱ ሲፈጸም መገኘት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሲሆን፤ ቤተሰቦችም ፍርዱ ለእነሱ አመቺ በሆነ ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚሉ ተነግሯል።
የሞት ፍርደኛው የነጭ የበላይነት አቀንቃኝ የነበረ ሲሆን የአንድ ቤተሰብ ሦስት አባላትን አሰቃይቶ ከገደለ በኋላ አስከሬናቸውን ሐይቅ ውስጥ በመጨመሩ ሞት ተፈርዶበት ባለፈው ታኅሳስ ወር ላይ ነበር ቅጣቱ ተግባራዊ ሊደረግበት የነበረው።
ነገር ግን ቅጣቱ እንዲዘገይ የተደረገው ፍርድ ቤቱ ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይደረግ የሚያዝ ውሳኔ በማሳለፉ ነበር ወንጀለኛው እስካሁን በሕይወት የቆየው።
ሴት ልጃቸውን፣ የልጅ ልጃቸውንና የልጃቸው ባል በግድያው ያጡት ኧርሊን ፒተርሰን ግን ወንጀለኛው በመርዝ መርፌ ተወግቶ መገደሉን ተቃውመውታል።
ለሲኤን ኤን እንተናገሩትም "በልጄ ምክንያት የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱ ለእሷ አሳፋሪ ነገር ነው" ሲሉ ወንጀለኛው እንዳይገደል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በሐምሌና በነሐሴ ወር ተግባራዊ እንዲደረጉ ከታሰቡት አራት የሞት ፍርዶች መካከል የዳንኤል ልዊስ አንዱ ሲሆን አራቱም ወንጀለኞች ወንዶችና ህጻናትን በመግደል የተፈረደባቸው ናቸው።
የሞት ቅጣትን በሚመለከት ያሉ መረጃዎችን የሚያሰባስበው ማዕከል እንዳለው እንደ አውሮፓውያኑ በ1988 እና በ2018 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ 78 ሰዎች በአሜሪካ ፌደራል መንግሥቱ በቀረበባቸው ክስ ሞት ተፈርዶባቸዋል።
ነገር ግን እስካሁን ሦስቱ ብቻ ነው ውሳኔው ተግባራዊ የተደረገባቸው፤ በአሁኑ ጊዜ 62 የሞት ፍርደኞች በፌደራሉ የዓለም በቃኝ እስር ቤቶች ውስጥ ቅጣታቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።












