ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮናቫይረስ ምክንያት የኤምሬትስ አየር መንገድ 9ሺህ ሠራተኞችን ሊቀንስ ነው
ኤምሬትስ አየር መንገድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ተጽእኖ ምክንያት ዘጠኝ ሺህ የሚደርሱ ሠራተኞቹን ሊቀንስ መሆኑን ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
የረጅም ርቀት ጉዞዎችን በማድረግ በዓለማችን ግዙፍ ከሚባሉት አየር መንገዶች አንዱ የሆነው ኤምሬትስ ይህን ያህል ሠራተኞችን ሊቀንስ መሆኑን ሲያስታውቅ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።
የኮሮናቫይረስ ተከስቶ የአየር ትራንስፖርቱን ዘርፍ ክፉኛ ከመጉዳቱ በፊት ኤምሬትስ 60,000 ሰራተኞች ነበሩት።
ፕሬዝዳንቱ ሰር ቲም ክላርክ አየር መንገዱ እስካሁን አንድ አስረኛ የሚሆኑትን ሠራተኞቹን መቀነሱን ጠቅሰው "ከዚህም በኋላ እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ተጨማሪ ሠራተኞችን ልንቀንስ እንችላልን" ሲሉ ተናግረዋል።
የአየር መንገዱ ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ እንደገለጹት ኮሮናቫይረስ በፈጠረው ችግር ምክንያት ኤምሬትስ "እንደ ሌሎቹ አየር መንገዶች በከፋ ሁኔታ አልተጎዳም" ብለዋል።
በአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ ውስጥ እየተወሰደ ያለው ሠራተኞችን የመቀነስ እርምጃ የኤምሬትስ ተቀጣሪዎችን ያሳሰባቸው ሲሆን ከዚህም ሊከፋ የሚችል እንደሆነም ሰግተዋል።
በኤምሬትስ ሠራተኞች በአየር መንገዱ ውስጥ ደካማ የመረጃ ልውውጥና የግልጽነት መጓደል አለ በሚል ቅሬታዎች እንዳሉ ቢቢሲ ተገንዝቧል።
እስካሁን ኤምሬትስ ካሉት 4,500 አብራሪዎች ውስጥ ቢያንስ 700 ለሚሆኑት ቅጥራቸው እንደሚቋረጥ በዚህ ሳምንት አሳውቋል። ይህም የኮሮናቫይረስ ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ቢያንስ 1,200 የሚደርሱት ከሥራ እንደሚቀነሱ ተነግሯቸዋል ማለት ነው።
በአብራሪዎቹ ላይ የተደረገው ከሥራ የመቀነስ ውሳኔ ያተኮረው ከቦይንግ አውሮፕላኖች ይልቅ በዋነኝነት ኤርባስ የተባሉትን አውሮፕላኖች በሚያበሩ ፓይለቶች ላይ ነው ተብሏል።
ከአብራሪዎቹ በተጨማሪ ኤምሬትስ በሺህዎች የሚቆጠሩ የበረራ ሠራተኞችንም እንደቀነሰ ተነግሯል።
ኤምሬት እጅግ ግዙፍ ከሆነውና 500 የሚደርሱ ሰዎችን ከሚያሳፍረው ሱፐርጃምቦ ኤርባስ ኤ380ኤስ አንስቶ የተለያየ ቁጥር ያላቸውን መንገደኞች እስከሚይዙት ቦይን 777 አውሮፕላኖች ድረስ አሉት።
290 አየር መንገዶች በአባልነት ያሉበት ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር እንደተነበየው በዚህ ዓመት ብቻ አየር መንገዶች ከ84 ቢሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ የሚገጥማቸው ሲሆን አንድ ሚሊዮን ሠራተኞችም ሥራቸውን ያጣሉ።