"ለኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታና የውሃ ሙሌት የተነጣጠሉ አይደሉም"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአመታት ሲደረግ የነበረው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ከሰሞኑም በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት እየተካሄደ ነው። ሶስቱ ተደራዳሪዎች፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳንም የደረሱበትንም ውሳኔ ለህብረቱ የሚያሳውቁ ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት ለድርድር ከመቀመጣቸው በፊትም ግብፅ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ኢትዮጵያ ውሃ ከመሙላት እንድትታቀብና የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤቱ ጣልቃ በመግባት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል በማለትም ባለ ስድሳ ሶስት ገፅ ደበብዳቤ አስገብታ ነበር።
በምላሹ ኢትዮጵያም የሦስትዮሽ ስምምነቱ ሳይጠናቀቅ ግብፅ ምክር ቤቱን ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም "ድርድሩ ፍሬ አልባ እንዲሆን እየሰራች ከነበረችው ግብፅ" የሚጠበቅ ነው በማለት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሪቬሬ በላኩት ደብዳቤ ገልፀዋል።
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም በበይነ መረብ ኮንፈረንስ በማድረግ አገራቱን አወያይቶ ነበር። በናይል ጉዳይ ላይ ተፋጥጠው ያሉት የግብፅና የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በዚህ ጉባኤም ወቅት ተጋግለው ታይተው ነበር ተብሏል።
ሁለቱም አገራት የህዝባችን ህልውና ነው በሚሉት ናይልን ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩም በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰማ ሲሆን በዚህም ጉባኤ ላይ ይኸው ነው የተንፀባረቀው።
ግብፅን ወክለው የቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሽኩሪ የናይል ውሃ የመቶ ሚሊዮን ግብፃውያን የመኖርና አለመኖር ጥያቄ ነው በሚል ሁኔታውን አቅርበዋል። በተመሳሳይ ድምፀትም በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታየ አፅቀ ስላሴም እንዲሁ ኢትዮጵያ ያሏትን የውሃ ሃብቶች መጠቀም ምርጫ ሳይሆን የአገሪቷ ህልውና መሰረት ነው ብለዋል።
የሁለቱ ሃገራት የቃላት የጦርነት ከአስር አመታት በላይ ዘሏል። በአመታትም ውስጥ በተደረጉ ድርድሮች ግድቡን በተመለከተ ስምምነቶች ላይ መድረስ ቢቻልም አሁንም የግድቡ ሙሌት፣ ልቄት የመሳሰሉት ነገሮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ሶስቱ ሃገራት ችግሮቻቸውንም ለመፍታት ከአምስት ዓመታት በፊት የህዳሴ ግድብ የትብብር መግለጫ ስምምነትም ቢፈርሙም ግብፅና ኢትዮጵያ ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ ስምምነቱን ጥሰሻል በሚልም እየተወነጃጀሉ ነው።
ኢትዮጵያ ያለሦስትዮሽ ስምምነት የግድቡን ሙሌት እጀምራለሁ ማለቷ የህዳሴ ግድብ የትብብር መግለጫ ስምምነትም የሚጥስና የታችኛው ተፋሰስ ሃገራትንም የሚጎዳ ነው ትላለች ግብፅ። ኢትዮጵያ በበኩሏ በታችኛው ተፋሰሰስ አገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስና የመጀመሪያ ደረጃ የግድቡ የውሃ ሙሌት መመሪያም የተወሰደው ሦስቱ አገራት ከተስማሙበት የግድብ ትብብር መግለጫ ስምምነት መሰረት ያደረገ ነው በሚል ትከራከራለች።
ኢትዮጵያ ያለ ሶስትዮሽ ስምምነት የውሃ ሙሌቱን በዚህ አመት የምትጀምር ሲሆን በእቅዷም መሰረት ሰባት አመታት ያህል ይፈጃል። ለኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ግንባታና የውሃ ሙሌቱ የተነጣጠሉ አይደለም የሚለው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ከሆኑት አንዱ ዘሪሁን አበበ ነው።
" ግብፅ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማወዛገብ ይህንን ትጠቀምበታለች" በማለት የሚናገረው ዘሪሁን ከአምስት አመታት በፊት አገራቱ የተፈራረሙትን የግድብ ትብብር መግለጫ ስምምነትም ውሃ ሙሌቱን እንድታከናውን ይፈቅድላታል ብሏል። ግብፅ ግን ሁኔታውን በዚህ መልኩ አይደለም የምትረዳው።
የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የሕግ እና የውሃ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሞያዎች በዋሽንግተን ዲሲ ሲደራደሩ በነበረበት ወቅት በዓመታት የተራዘመ ድርቅ እንዲሁም በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የውሃ ፍሰት ላይም መሰረታዊ መግባባት ተደርሷል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ያለምንም ውጤት መቋረጡ ይታወሳል።
በወቅቱም ግብጽ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቴን ይቀንሰዋል እንዲሁም ለእርሻ የሚያስፈልገኝ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በየዓመቱ ይገባኛል ስትል የቆየች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ 31 ቢሊዮን ኪዩቡክ ውሃ በዓመት ለመልቀቅ ሃሳብ አቅርባ ነበር። ነገር ግን አሜሪካ በበኩሏ 37 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር እንዲለቀቅ መጠየቋ ተነግሮ ነበር።
ኢትዮጵያ ወንዙ በግድቡ ስፍራ እንደሚኖረው ዓመታዊ የፍሰት መጠን ከ4 -7 ዓመታትን በሚወስድ የሙሌት ደረጃ ግድቡን የመሙላት እቅድን ብታቀርብም ግብፅጽ በበኩሏ ጥቅሜን የሚጋፋ ነው በማለት ከ12 እስከ 21 ዓመታት መውሰድ አለበት ትላለች።
ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረውንም ድርድር ያቋረጠችበት ምክንያት በግብጽ ፍላጎት ታዛቢ እንዲሆኑ የገቡት አሜሪካና የዓለም ባንክ ለግብጽ ከመወገን አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል በማለት ኢትዮጵያ መውቀሷ የሚታወስ ነው።
አሜሪካ፣ የዓለም ባንክ ከግብጽ ጎን ቆመው ነበር በተባለው በዚህ ድርድር ላይ ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጾ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የግብጽ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ትተቻለች።

የፎቶው ባለመብት, US president's office
የቅኝ ግዛት ስምምነት
ግብፅ የምትጠቅሰው የመጀመሪያ ስምምነት የተፈረመው በጎርጎሳውያኑ 1929 ሲሆን በወቅቱ የነበረችው ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝም ግብፅ በናይል ውሃ ላይ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት እንዳላት ከማረጋገጥ በተጨማሪ የላይኛው ተፋሰስ ሃገራትን በተመለከተ ፈላጭ፣ ቆራጭ አድርጓታል።
በኋላም በጎርጎሳውያኑ 1959 በሱዳንና ግብፅ የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት አጥብቃ በመያዝ፣ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርህ፣ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላትና ሙጥኝ ማለቷንም በመጥቀስ ኢትዮጵያ ትወቅሳለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች የዘጠኝ ተፋሰስ ሃገራትን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብጽ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንድታገኝና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይና ኢፍትሃዊ ስምምነት ነውም ትላለች።
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሃብቷን አለመጠቀሟ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት እንደተፈፀመባት እንደምታየው ዘሪሁን ይናገራል። ኢትዮጵያ በየአመቱ የምትለቀውን ውሃ በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረስ ማለት "የታችኛው ተፋሰስ ሃገር የሆነችው ግብፅ አለኝ የምትለውን የቅኝ ግዛት ጥቅም ጋር መስማማት ነው። ይህ ማለት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነው፤ ተቀባይነት የለውም" ይላል።
በሌላ መልኩ ግብፅ አሁንም በጎርጎሳውያኑ 1959 የተፈረመውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ በማለት ያንኑ ለማስፈፀምም እንደምትሰራ ኢትዮጵያ ትናገራለች።
የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በአባይ ወንዝ ለዘመናት ሲቆጭ የነበረ ህዝብ ለህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም ከመሃረባቸው ሳይቀር እየፈቱ፣ ያለች የሌለቻቸውን ቤሳ ቤስቲን ያዋጡ በርካቶች ናቸው። እስካሁንም ድረስ ለግድቡ ግንባታ 4 ቢሊዮን ዶላርም ወጥቷል።
የሰሞኑን የህዝቡን መንፈስ የሚያንፀባርቅም ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መወያያ ሆኖ ነበር። በቲክቶክ ላይ አንደኛዋ ኢትዮጵያዊት ውሃ የተሞላ ጆግ ይዛ በብርጭቆ ለሱዳንና ለግብፅ ለማከፋፈል ትሞክርና የግብፅን ድርሻ መልሳ በመውሰድ ብርጭቆውን በለበሰችው ልብስ በመጥረግ ኢትዮጵያ የአባይ መነሻ መሆኗንና የመንጠቅ መብት አላትም የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ሞክራለች።
ግብፆችም በበኩላቸው ግድቡን ማጥቃት እንችላለን በሚል ዛቻ አስተላልፈዋል። የግብፅ ሚዲያም የመንግሥታቸውን አቋም በመደገፍ ይታወቃሉ።















