የብሔራዊ ፈተና ውጤትና የተማሪዎች ማንነት የሚሰረቅባት ቻይና

ቼን ቹንሁ የአርሶ አደር ልጅ ናት። ጋዎኮ የሚባለውን የቻይና ብሔራዊ ፈተናን አልፋ ዩኒቨርስቲ የመግባት ህልም ነበራት። ፈተናውን ስለወደቀች ያለመችው ሳይሳካ ቀረ።

ኮሌጅ መግባት ስላልቻለች ያገኘችውን ትሠራ ጀመር። ፋብሪካ ተቀጥራለች፤ አስተናጋጅ ሆናም ነበር። ኋላ ላይ በመዋለ ሕጻናት ውስጥ ማስተማር ጀመረች።

ከ16 ዓመታት በኋላ ግን ያልጠበቀችው ዜና ደረሳት። ለካስ ሻንዶንግ ዩኒቨርስቲ ሊቀበላት ፍቃደኛ ነበር። ነገር ግን የእሷን ስምና አጠቃላይ ማንነት የሰረቀች አንዲት ተማሪ በስሟ ዩኒቨርስቲውን ተቀላቅላለች።

ተማሪዋ የቼንን ማንነት ሰርቃ፣ ቼንን መስላ ዩኒቨርስቲ እንድትገባ ያመቻቹት ቤተሰቦቿ ነበሩ።

እንደዚህ ባለ መንገድ የተጭበረበረችው ቼን ብቻ አይደለችም። ሌሎች 242 ተማሪዎችም ማንነታቸው ተሰርቋል። የእነዚህን ተማሪዎች ስም ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መገለጫዎቻቸውን በማስመሰል ዩኒቨርስቲ የገቡ ሰዎች 242 ናቸው ማለት ነው።

ማጭበርበሩ የተፈጸመው በቻይናዋ ሻንዶንግ ግዛት እአአ ከ2002 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት ነበር።

አስደንጋጩ የማንነት ስርቆት

የቻይናው ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ጋዎኮ የሚሰጠው በሒሳብ፣ በእንግሊዝኛ፣ በማንዳሪን እና በሌሎችም የትምህርት ዘርፎች ነው። ተማሪዎች ምን መፈተን እንደሚፈልጉ መምረጥ ይችላሉ። ፈተናው እጅግ ከባድ እንደሆነም ይነገርለታል።

ቤተሰቦቻቸው አነስተኛ ገቢ ያላቸው ታዳጊዎች ፈተናው ሕይወታቸውን እንደሚቀይር ተስፋ ያደርጋሉ።

የቼን ቤተሰቦችም ልጃችን ዩኒቨርስቲ ገብታ እኛም ያልፍልናል ብለው ተስፋ ጥለው ነበር። ድሃ ስለሆኑ ከሁለት ልጆቻቸው መካከል ቼንን ብቻ ነበር ማስተማር የቻሉት።

2004 ላይ ቼን ጋዎኮ ተፈተነች። ዩኒቨርስቲው ደብዳቤ ስላልላከላት ፈተናውን እንደወደቀች አመነች።

ከዓመታት በኋላ በመንግሥት ድረ ገጽ ለመማር ተመዘገበች። 2004 ላይ ዩኒቨርስቲ ገብታ 2007 ላይ እንደተመረቀች ድረ ገጹ ሲነግራት ግን ግራ ተጋባች።

ድረ ገጹ ላይ ያለው ፎቶግራፍ የእሷ አልነበረም።

ዢንዋ እንደዘገበው፤ የቼንን ስምና የብሔራዊ ፈተና ውጤቷን ለእህቱ ልጅ የሰጠው ግለሰብ አንድ ባለሥልጣን ነው።

ቼን ከ750- 546 ስታመጣ፤ የቼንን ውጤት የሰረቀችው ተማሪ ግን 303 ነበር ያገኘችው።

ዩኒቨርስቲው ለቼን የጻፈውን ደብዳቤ ባለሥልጣኑ ከፖስታ ቤት አሰርቋል። የሁለተኛ ደረጃ ውጤቷን በመመዝበርም የእህቱን ልጅ ስም በቼን ቦታ ተክቷል።

በወንጀሉ የተሳተፉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱና ፖስታ ቤቱ ብቻ አልነበሩም። ፖሊስና የሻንዶንግ ዩኒቨርስቲ ሠራተኞችም ነገሩን ለማደባበስ ተስማምተዋል።

ቼን ያንፒንግ የተባለችው ተማሪ የእውነተኛዋን ቼን ቹንሁን ማንነት የዘረፈችው በዚህ ጥልፍልፍ መንገድ ነበር።

የቼንን ማንነት የሰረቀችው ሌላዋ ቼን አሁንም የእውነተኛዋን ቼን ሙሉ ስም ነው የምትጠቀመው። የሥራ ባልደረቦቿም ቼን ቹንሁ ብለው ነው የሚጠሯት።

የማንነት ስርቆት እንደፈጸመች በመገናኛ ብዙሃን ከተገለጸ በኋላ ከሥራ ተባራለች፤ ዲግሪዋንም ተቀምታለች። መንግሥት ምርመራ እያደረገባትም ይገኛል።

እውነተኛዋ ቼን ከሲሲቲቪ ጋር ባደረገችው ቆይታ “ለምን ማንነቴን እንደሰረቀችኝ በአካል አግኝቼ ልጠይቃት እፈልጋለሁ።” ብላለች።

“እኔን ምን እንዲውጠኝ ነው? ምን አይነት ራስ ወዳድ ነሽ?”

ቼን ከሲሲቲቪ ጋር ቃለ ምልልስ ስታደርግ ማንነቷን ለሰረቀችው ቼን “ተካሽኝ፤ እኔን ምን እንዲውጠኝ ነው? ምን አይነት ራስ ወዳድ ሰው ነሽ?” ብላታለች።

የቼን ታሪክ በርካቶችን አስቆጥቷል። ለዓመታት ተግተው የተማሩ ታዳጊዎች አቅመ ደካማ በመሆናቸው ብቻ ውጤታቸው መሰረቁ የብዙዎችን ልብ ሰብሯል።

በቻይና የትምህርትና የሳይንስ ተቋም ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ቹ ዛሆይ እንደሚሉት፤ ብሔራዊ ፈተናን በተመለከተ ሁለት አይነት የማጭበርበሪያ መንገዶች አሉ።

አንደኛው ማንነቱን የሚሰረቀው ሰው ስለ ጉዳዩ ምንም መረጃ ሳይኖረው የሚካሄድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ግለሰቡ ማንነቱን ለሌላ ሰው አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቶ የሚከናወን ሽያጭ ነው።

ተመራማሪዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ “የመጀመሪያው ዩኒቨርስቲ በመመዝገብ ሂደት ውስጥ ያሉ አካላት በሙሉ ተባብረው የሚፈጽሙት ማጭበርበር ነው። ይህም ትምህርት ቤቱን፣ የፈተና አውጪ ድርጅቱን እንዲሁም መዝጋቢዎችን ያካትታል።”

መሰል የማንነት ምዝበራ በዋነኛነት ጫና የሚያሳድረው አቅመ ደካሞች ላይ ነው።

አርሶ አደሩ የቹን አባትም ያሉት ተመሳሳይ ነገር ነው። “አርሶ አደር ምን ማድረግ ይችላል? ሀብታም ብሆን ይሄንን ለማድረግ አይደፍሩም ነበር” ብለዋል ለቻይና መገናኛ ብዙሃን።

በአገሪቱ ምክር ቤት፤ በማንነት ስርቆት ዩኒቨርስቲ የመግባት ሂደት ወንጀል ተብሎ እንዲመደብ ተጠይቋል።

የሻንዶንግ ባለሥልጣኖች፤ ከዚህ በኋላ ተማሪዎች የሌላ ሰው ውጤት ሰርቀው ዩኒቨርስቲ እንዳይገቡ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

ተማሪዎች ደብዳቤ፣ መታወቂያ፣ መኖሪያ ፍቃድና ፈተናውን መውሰዳቸውን የሚያሳይ ሰነድ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ዝርዝር በድረ ገጽ ይለጠፋል። ለተማሪዎቹም በስልካቸው የጽሁፍ መልዕክት ይላካል።

የትምህርት ሚንስቴር ማንነት የሚሰርቁ ተማሪዎችን ዩኒቨርስቲዎች እንደማይቀበሉ አስታውቋል።

አሁን ላይ የቼንን ጨምሮ የ46 ተማሪዎች ጉዳይ እየተመረመረ ነው።

ቼን የተሰረቀችውን ሕይወት ለማካካስ እየሞከረች ሲሆን ወደ ሻንዶንግ ዩኒቨርስቲ ለመግባት በድጋሚ አመልክታለች።

የመጀመሪያ ጥያቄዋን ዩኒቨርስቲው ባለመቀበሉ በርካቶች ተበሳጭተው ነበር። ይህን ተከትሎም ዩኒቨርስቲው “የቼንን ህልም እውን ለማድረግ እየሞከርን ነው” ብለዋል።